1 እናንት ዕረፍት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፤
በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም፤
2 የተወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣
ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣
የእግዚአብሔርጽኑ ቊጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣
የእግዚአብሔርየመዓት ቀን
ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ።
3 እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣
ትእዛዙን የምትፈጽሙ፣እግዚአብሔርንእሹ፤
ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤
በእግዚአብሔርየቊጣ ቀን፣
ትሰወሩ ይሆናል።
በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ጥፋት
4 ጋዛ ባድማ ትሆናለች፤
አስቀሎናም ፈራርሳ ትቀራለች፤
አዛጦን በቀትር ባዶ ትሆናለች፤
አቃሮንም ትነቀላለች።
5 እናንት በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፣
የከሊታውያን ሰዎች ሆይ፤ ወዮላችሁ
የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፤
በአንቺ ላይ የተነገረውየእግዚአብሔርቃል ይህ ነው፤
“ፍጹም አጠፋሻለሁ፤
ከነዋሪዎችሽም የሚተርፍ የለም።”
6 የቀርጤስሰዎች የሚኖሩበት በባሕሩ
ዳር ያለው ምድር፣
የእረኞች መኖሪያና የበጎች በረት ይሆናል፤
7 ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤
እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ።
በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም፣
በምሽት ይተኛሉ፤
አምላካቸውእግዚአብሔርይጠብቃቸዋል፤
ምርኮአቸውንም ይመልስላቸዋል።
በሞዓብና በአሞን ላይ የተነገረ ጥፋት
8 “የሞዓብን ስድብ፣
የአሞናውያንንም ፌዝ ሰምቻለሁ፤
ሕዝቤን ሰድበዋል፤
በምድራቸውም ላይ ዝተዋል።
9 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ ሁሉን የሚገዛእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“በሕያውነቴ እምላለሁ
ሞዓብ እንደ ሰዶም፣
አሞናውያን እንደ ገሞራ፣
ዐረም እንደ ዋጠው ቦታና እንደ ጨው
ጒድጓድ ለዘላለም ጠፍ ይሆናሉ።
ከሕዝቤ የቀሩት ይዘርፏቸዋል፤
ከወገኔ የተረፉትም ምድራቸውን
ይወርሳሉ።”
10 ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤
የሁሉን ገዥየእግዚአብሔርንሕዝብ
ሰድበው ዘብተውበታልና፣
11 እግዚአብሔርየምድሪቱን አማልክት
ሁሉ በሚደመስስበት ጊዜ፣
በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤
በየባሕሩ ጠረፍ የሚኖሩ ሕዝቦች፣
እያንዳንዳቸው በያሉበት ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ጥፋት
12 “ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ እናንተም፣
በሰይፌ ትገደላላችሁ።”
በአሦር ላይ የተነገረ ጥፋት
13 እጁን በሰሜን ላይ ይዘረጋል፤
አሦርንም ያጠፋል፤
ነነዌን ፍጹም ባድማ፣
እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል።
14 የበግና የከብት መንጋዎች፣
የፍጥረት ዐይነት ሁሉ በውስጧ ይመሰጋሉ፤
ጒጒትና ጃርት፣
በግንቦቿ ላይ ያድራሉ።
ጩኸታቸው በየመስኮቱ ያስተጋባል፤
ፍርስራሽ በየደጃፉ ይከመራል፤
ከዝግባ የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይገለጣሉ።
15 ተዘልላ የኖረች፣
ደስተኛዪቱ ከተማ ይህች ናት፤
እርሷም በልቧ፣
“እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ማንም የለም” ያለች፣
ታዲያ እንዴት የዱር አራዊት የሚመሰጉባት፣
ባድማ ሆና ቀረች?
በአጠገቧ የሚያልፉ ሁሉ፣
ያፌዙባታል፤ እጃቸውንም በንቀት ያወዛውዙባታል።