የኢየሩሳሌም የወደ ፊት ዕጣ
1 ለዐመፀኛዪቱና ለረከሰች፣
ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት!
2 እርሷ ለማንም አትታዘዝም፤
የማንንም ዕርምት አትቀበልም፤
በእግዚአብሔርአትታመንም፤
ወደ አምላኳም አትቀርብም።
3 ሹሞቿ የሚያገሡ አንበሶች፣
ገዦቿ ለነገ የማይሉ፣
የምሽት ተኵላዎች ናቸው።
4 ነቢያቷ ትዕቢተኞች፣
አታላዮችም ናቸው፤
ካህናቷ መቅደሱን ያረክሳሉ፣
በሕግም ላይ ያምፃሉ።
5 በእርሷ ውስጥ ያለውእግዚአብሔርጻድቅ ነው፤
ፈጽሞ አይሳሳትም፤
በየማለዳው ቅን ፍርድ ይሰጣል፤
በየቀኑም አይደክምም፤
ዐመፀኞች ግን ዕፍረት አያውቁም።
6 “ሕዝቦችን አጥፍቻለሁ፤
ምሽጋቸው ተደምስሶአል፤
ማንም እንዳያልፍባቸው፣
መንገዳቸውን ባድማ አደረግሁ፤
ከተሞቻቸው ተደምስሰዋል፤
አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም ከቶ አይገኝባቸውም።
7 እኔም ከተማዪቱን፣
‘በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፤
ዕርምትም ትቀበያለሽ’ አልኋት፤
ስለዚህ መኖሪያዋ አይጠፋም፤
ቅጣቴም ሁሉ በእርሷ ላይ አይደርስም።
እነርሱ ግን በሚያደርጉት ሁሉ፣
ክፋትንም በመፈጸም እየተጉ ሄዱ።
8 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ስለዚህ እስከምፈርድበትቀን ድረስ
ጠብቁኝ፤
አሕዛብን ላከማች፣
መንግሥታትን ልሰበስብ፣
መዓቴንና ጽኑ ቊጣዬን፣
በላያቸው ላፈስ ወስኛለሁ፤
በቅናቴ ቍጣ እሳት፣
መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።
9 “በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉየእግዚአብሔርንስም እንዲጠሩ፣
ተስማምተው እንዲያገለግሉት፣
አንደበታቸውን አጠራለሁ።
10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ፣
የሚያመልኩኝ፣ የተበተኑት ሕዝቤ
ቊርባን ያመጡልኛል።
11 በእኔ ላይ ከፈጸማችሁት በደል ሁሉ የተነሣ፣
በዚያ ቀን አታፍሩም፤
በትዕቢታቸው የሚደሰቱትን፣
ከዚህች ከተማ አስወግዳለሁና፤
ከእንግዲህ ወዲያ፣
በቅዱስ ተራራዬ ላይ አትታበዩብኝም።
12 በእግዚአብሔርስም የሚታመኑትን፣
የዋሃንንና ትሑታንን፣
በመካከላችሁ አስቀራለሁ።
13 የእስራኤል ትሩፋን ኀጢአት አይሠሩም፤
ሐሰትም አይናገሩም፤
በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም።
ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤
የሚያስፈራቸውም የለም።
14 የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ፤
እስራኤል ሆይ፤ እልል በይ፤
የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤
በፍጹም ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ።
15 እግዚአብሔርቅጣትሽን አስወግዶታል፤
ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሶአል፤
የእስራኤል ንጉሥእግዚአብሔርከአንቺ ጋር ነው፤
ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም።
16 በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን እንዲህ
ይሏታል፤
“ጽዮን ሆይ፤ አትፍሪ፤
እጆችሽም አይዛሉ።
17 እግዚአብሔርአምላክሽ በመካከልሽ አለ፤
እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤
በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤
በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤
በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
18 “ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣
የስድብሽን ሸክም፤
ከአንቺ አስወግዳለሁ።
19 በዚያ ጊዜ፣
ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤
አንካሶችን እታደጋለሁ፤
የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤
በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣
ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ።
20 በዚያን ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤
ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤
ዐይናችሁ እያየ፣
ምርኮአችሁን በምመልስበት ጊዜ፣
መከበርንና መወደስን፣
በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤
ይላልእግዚአብሔር።