ናሆም 1

1 ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤

በነነዌ ላይ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቍጣ

2 እግዚአብሔርቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤

እግዚአብሔርየሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው።

እግዚአብሔርባላጋራዎቹን ይበቀላል፤

በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል

3 እግዚአብሔርለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ ነው፤

እግዚአብሔርበደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤

መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤

ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።

4 ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤

ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል።

ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤

የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።

5 ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤

ኰረብቶችም ቀለጡ።

ምድር በፊቱ፣

ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።

6 ቊጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል?

ጽኑ ቊጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል?

መዓቱ እንደ እሳት ፈሶአል፤

ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።

7 እግዚአብሔርመልካም ነው፤

በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው።

ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤

8 ነነዌን ግን፣

በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤

ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።

9 በእግዚአብሔርላይ ምንም ቢያሤሩ፣

እርሱ ያጠፋዋል፤

መከራም ዳግመኛ አይነሣም።

10 በእሾህ ይጠላለፋሉ፤

በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤

እሳትም እንደ ገለባይበላቸዋል።

11 ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣

ክፋትንም የሚመክር፣

ከአንቺ ዘንድ ወጥቶአል።

12 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣

ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም።

ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣

ከእንግዲህ አላስጨንቅህም።

13 አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤

የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።”

14 አንቺ ነነዌ፤እግዚአብሔርስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዞአል፤

“ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤

በአማልክቶቻችሁ ቤት ያሉትን፣

የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤

መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤

አንተ ክፉ ነህና።

15 እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣

ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣

በተራሮች ላይ ነው፤

ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር፤

ስእለትህንም ፈጽም፤

ከእንግዲህ ክፉዎች አይወሩህም፤

እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *