በእስራኤል ላይ የተጠሩ ምስክሮች
1 የእስራኤል ልጆች ሆይ፤እግዚአብሔርበእናንተ ከግብፅ ባወጣሁት ሕዝብ ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤
2 “ከምድር ወገን ሁሉ፣
እናንተን ብቻ መረጥሁ፤
ስለዚህ ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፣
እኔ እቀጣችኋለሁ።”
3 በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ፣
አብረው መጓዝ ይችላሉን?
4 አንበሳ የሚበላውን ሳያገኝ፣
በጫካ ውስጥ ይጮኻልን?
ምንም ነገርስ ሳይዝ፣
በዋሻው ውስጥ ያገሣልን?
5 ወጥመድ ሳይዘረጋ፣
ወፍ በምድር ላይ ይጠመዳልን?
የሚይዘው ነገር ሳይኖርስ፣
ወጥመዱ ከምድር ይፈነጠራልን?
6 የመለከት ድምፅ በከተማ ውስጥ ሲሰማ፣
ሰዎች አይደነግጡምን?
ጥፋትስ በከተማ ላይ ቢደርስ፣
ያደረገውእግዚአብሔርአይደለምን?
7 በእውነት ጌታእግዚአብሔርምስጢሩን
ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣
ምንም ነገር አያደርግም።
8 አንበሳ አገሣ፤
የማይፈራ ማን ነው?
ጌታእግዚአብሔርተናገረ፤
ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
9 ለአዛጦን ምሽግ፣
ለግብፅም ምሽግ እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤
“በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፤
በውስጧ ያለውን ታላቅ ሁከት፣
በሕዝቧም መካከል ያለውን ግፍ እዩ።”
10 “ቅሚያንና ዝርፊያን በምሽጋቸው ውስጥ የሚያከማቹ፣
በጎ ነገር ማድረግን አያውቁም፤”
ይላል እግዚአብሔር።
11 ስለዚህ ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ጠላት ምድሪቱን ይወራል፤
ምሽጎቻችሁን ያፈርሳል፤ ድንኳኖቻችሁን
ይዘርፋል።”
12 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እረኛ ከአንበሳ መንጋጋ፣
ሁለት የእግር ዐጥንት ወይም የጆሮ ቍራጭ እንደሚያድን፣
እንዲሁም በሰማርያ በዐልጋቸውጫፍ ላይ፣
በደማስቆም በምንጣፋቸው ላይ የተቀመጡ፣
እስራኤላውያን ይድናሉ።”
13 “ይህን ስሙ፤ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ” ይላል ጌታ፣ ሁሉን የሚገዛ አምላክእግዚአብሔር።
14 “እስራኤልን ስለ ኀጢአቷ በምቀጣበት ቀን፣
የቤቴልን መሠዊያዎች አፈርሳለሁ፤
የመሠዊያው ቀንዶች ይቈረጣሉ፤
ወደ ምድርም ይወድቃሉ።
15 የክረምቱን ቤት፣
ከበጋው ቤት ጋር እመታለሁ፤
በዝሆን ጥርስ ያጌጡ ቤቶችም ይደመሰሳሉ፤
ታላላቅ አዳራሾችም ይፈርሳሉ፤”
ይላልእግዚአብሔር።