በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት
1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ያየው ንግር፤
2 በተራቈተ ኰረብታ ዐናት ላይ ምልክት ስቀሉ፤
ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ፤
በመሳፍንቱም በር እንዲገቡ፣
በእጅ ምልክት ስጡ።
3 በድል አድራጊነቴ ደስ የሚላቸውን ቅዱሳኔን አዛለሁ፤
ቍጣዬንም እንዲፈጽሙ፣
ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ።
4 በተራሮች ላይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣
የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ
በመንግሥታትም መካከል፣
እንደ ተጨናነቀ ሕዝብ ድምፅ የሆነውን ውካታ ስሙ!
የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር
ሰራዊቱን ለጦርነት አሰልፎአል።
5 እግዚአብሔርናየቍጣው ጦር መሣሪያ፣
ምድሪቱን በሙሉ ለማጥፋት፣
ከሩቅ አገር፣
ከሰማያትም ዳርቻ መጥተዋል።
6 የእግዚአብሔርቀን ቀርቦአልና አልቅሱ፤
ሁሉን ቻይከሆነ አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣልና።
7 ስለዚህ እጆች ሁሉ ሽባ ይሆናሉ፤
የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።
8 ሽብር ይይዛቸዋል፤
ሥቃይና ጭንቀት ይደርስባቸዋል፤
ምጥ እንደ ያዛት ሴት ያምጣሉ፤
እርስ በርሳቸው በድንጋጤ ይተያያሉ፤
ፊታቸውም በፍርሀት ቀይ ይሆናል።
9 እነሆ፤የእግዚአብሔርቀን ጨካኝ ነው፤
ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፣
በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣
ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋር ይመጣል።
10 የሰማይ ከዋክብትና ሰራዊታቸው፣
ብርሃን አይሰጡም፤
ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤
ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።
11 ዓለምን ስለ ክፋቷ፣
ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤
የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤
የጨካኞችንም ጒራ አዋርዳለሁ።
12 ሰውን ከነጠረ ወርቅ ይልቅ ውድ፣
ከኦፊርም ወርቅ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።
13 ስለዚህ በሰራዊት ጌታበእግዚአብሔርመዓት፣
ቍጣው በሚነድበት ቀን፣
ሰማያትን እነቀንቃለሁ፤
ምድርንም ከስፍራዋ አናውጣለሁ።
14 እንደሚታደን ሚዳቋ፣
እረኛም እንደሌለው የበግ መንጋ፣
እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፣
እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።
15 የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤
የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።
16 ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤
ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።
17 እነሆ፤ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣
በወርቅም ደስ የማይሰኙትን፣
ሜዶናውያንን አስነሣባቸዋለሁ።
18 ቀስታቸው ጐበዞችን ይፈጃል፤
ሕፃናትን አይምሩም፤
ዐይናቸውም ለልጆች አይራራም።
19 የመንግሥታት ዕንቍ፣
የከለዳውያንትምክሕት፣
የሆነችውን ባቢሎንን፣
እግዚአብሔርእንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል።
20 በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤
የሚቀመጥባትም የለም
ዐረብ በዚያ ድንኳኑን አይተክልም፤
እረኛም መንጋውን በዚያ አያሳርፍም።
21 ነገር ግን የምድረ በዳ አራዊት በዚያ ይተኛሉ፤
ቀበሮዎች ቤቶቿን ይሞላሉ፤
ጒጒቶች በዚያ ይኖራሉ፤
በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም ይዛለሉበታል።
22 ጅቦች በምሽጎቿ፣
ቀበሮዎችም በተዋቡ ቤተ መንግሥቶቿ ይጮኻሉ፤
ጊዜዋ ቀርቦአል፤
ቀኗም አይራዘምም።