1 እግዚአብሔርለያዕቆብ ይራራለታል፤
እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤
በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል።
መጻተኞች አብረዋቸው ይኖራሉ፤
ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተባበራሉ።
2 አሕዛብም ይወስዷቸዋል፤
ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል።
የእስራኤል ቤት አሕዛብን ርስት ያደርጓቸዋል፤
በእግዚአብሔርምምድር ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች አድርገው ይገዟቸዋል፤
የማረኳቸውን ይማርኳቸዋል፤
የጨቈኗቸውንም ይገዟቸዋል።
3 እግዚአብሔርከሥቃይህ፣ ከመከራህና ከጽኑ ባርነትህ ባሳረፈህ ቀን፣
4 በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሣለቃለህ፤ እንዲህም ትላለህ፤
ጨቋኙ እንዴት አበቃለት!
አስገባሪነቱስእንዴት አከተመ!
5 እግዚአብሔርየክፉዎችን ዘንግ፣
የገዦችንም በትረ መንግሥት ሰብሮአል፤
6 ሕዝቦችን በማያቋርጥ ቍጣ የመታውን፣
ያለ ርኅራኄ እያሳደደ
የቀጠቀጠውን ሰብሮአል።
7 ምድር ሁሉ ሰላምና ዕረፍት አግኝታለች፤
የደስታም ዝማሬ ታስተጋባለች።
8 ጥድና የሊባኖስ ዝግባ እንኳ ደስ ብሎአቸው፣
“አንተም ወደቅህ፤
ዕንጨት ቈራጭም
መጥረቢያ አላነሣብንምቃ አሉ።
9 በመጣህ ጊዜ
ሲኦልልትቀበልህ ተነሣሥታለች፤
ይቀበሉህም ዘንድ የሙታንን መናፍስት፣
በዓለም ገዥ የነበሩትን ሁሉ ቀስቅሳለች፤
በአሕዛብ ላይ የነገሡትን ነገሥታት
ከዙፋናቸው አውርዳለች።
10 እነርሱ ሁሉ ይመልሱልሃል፤
እንዲህም ይሉሃል፤
“አንተም እንደ እኛ ደከምህ፤
እንደ እኛም ሆንህ።”
11 ክብርህ፣ ከነበገና ድምፁ
ወደ ሲኦል ወረደ፤
ብሎች ከበታችህ ተነጥፈዋል፤
ትሎችም መደረቢያህ ይሆናሉ።
12 አንተ የንጋት ልጅ፣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፤
እንዴት ከሰማይ ወደቅ
አንተ ቀድሞ መንግሥታትን ያዋረድህ፤
እንዴት ወደ ምድር ተጣልህ!
13 በልብህም እንዲህ አልህ፤
“ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤
ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤
በተራራው መሰብሰቢያ፣
በተቀደሰውም ተራራከፍታ ላይ በዙፋኔ
እቀመጣለሁ፤
14 ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤
ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።”
15 ነገር ግን ወደ ሲኦል፣
ወደ ጥልቁም ጒድጓድ ወርደሃል።
16 የሚያዩህም አትኵረው እየተመለክቱህ፣
በመገረም ስለ አንተ እንዲህ ይላሉ፤
“ያ ምድርን ያናወጠ፣
መንግሥታትን ያንቀጠቀጠ፣ ይህ ሰው ነውን?
17 ዓለምን ምድረ በዳ ያደረገ፤
ከተሞችን ያፈራረሰ፣
ምርኮኞቹንም ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ የከለከለ ይህ ነውን?”
18 የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በክብር አንቀላፍተዋል፤
በየመቃብራቸው ዐርፈዋል።
19 አንተ ግን እንደማይፈለግ ቅርንጫፍ፣
ከመቃብር ወጥተህ ተጥለሃል፤
በሰይፍ በተወጉት፣
ወደ ጥልቁ ድንጋዮች በወረዱት፣
በተገደሉትም ተሸፍነሃል።
እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።
20 ከእነርሱ ጋር በመቃብር አትሆንም፤
ምድርህን አጥፍተሃልና፤
ሕዝብህንም ፈጅተሃልና።
የክፉ አድራጊዎች ዘር
ፈጽሞ አይታወስም።
21 ተነሥተው ምድርን እንዳይወርሱ፣
ዓለምንም በከተሞቻቸው እንዳይሞሉ፣
ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት፣
ወንድ ልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።
22 “በእነርሱ ላይ እነሣለሁ”
ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።
“ስሟንና ትሩፋኖቿን፣
ዘሯንና ትውልዷን ከባቢሎን እቈርጣለሁ”
ይላልእግዚአብሔር።
23 “የጃርት መኖሪያ፣
ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤
በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ”
ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።
በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት
24 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ብሎ ምሎአል፤
“እንደ ዐቀድሁት በርግጥ ይከናወናል፤
እንደ አሰብሁትም ይሆናል።
25 አሦርን በምድሬ ላይ አደቃለሁ፤
በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤
ቀንበሩ ከሕዝቤ ላይ ይነሣል፤
ሸክሙም ከትከሻቸው ላይ ይወርዳል።”
26 ለምድር ሁሉ የታሰበው ዕቅድ ይህ ነው፤
በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋው እጅ ይኸው ነው።
27 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ አስቦአል፤
ማንስ ያግደዋል?
እጁም ተዘርግቶአል?
ማንስ ይመልሰዋል?
በፍልስጥኤማውያን ላይ የተነገረ ትንቢት
28 ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት እንዲህ የሚል ንግር መጣ፤
29 “እናንት ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤
የመታችሁ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁ ደስ አይበላችሁ፤
ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፤
ፍሬውም ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ ይሆናል።
30 ከድኻም ድኻ የሆኑት መሰማሪያ ያገኛሉ፤
ችግረኞችም ተዝናንተው ይተኛሉ፤
ሥርህን ግን በራብ እገድላለሁ፤
ትሩፋንህንም እፈጃለሁ።
31 በር ሆይ፣ ዋይ በል፤ ከተማ ሆይ ጩኽ፣
ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ ሁላችሁም በፍርሀት ቅለጡ
ጢስ ከሰሜን መጥቶብሃል፤
ከሰልፉ ተነጥሎ የሚቀር የለምና።
32 ከዚያ ሕዝብ ለሚመጡ መልእክተኞች ምን መልስ ይሰጣል?
መልሱ፣ “እግዚአብሔርጽዮንን መሥርቶአል፤
መከራን የተቀበለው ሕዝብም፣
በእርሷ ውስጥ መጠጊያን አግኝቶአል” የሚል ነው።