በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት
1 ስለ ሞዓብ የተነገረው ንግር ይህ ነው፤
የሞዓብ ዔር ፈራረሰች፤
በአንድ ሌሊትም ተደመሰሰች።
የሞዓብ ቂር ፈራረሰች፣
በአንድ ሌሊት ተደመሰሰች።
2 ዲቦን ወደ መቅደሱ ወጣ፤
ሊያለቅስም ወደ ኰረብታው ሄደ፤
ሞዓብ ስለ ናባው፣ ስለ ሜድባም ዋይታ ያሰማል፤
ራስ ሁሉ ተመድምዶአል፤
ጢምም ሁሉ ተላጭቶአል።
3 በየመንገዱም ማቅ ይለብሳሉ፤
በየሰገነቱና በየአደባባዩ
ሁሉም ያለቅሳሉ፤
እንባም ይራጫሉ።
4 ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤
ድምፃቸው እስከ ያሀድ ድረስ ተሰማ፤
ስለዚህ የሞዓብ ጦረኞች ጮኹ፤
ልባቸውም ራደ።
5 ልቤ ስለ ሞዓብ አለቀሰ፤
ስደተኞቿም እስከ ዞዓር፣
እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ሸሹ፤
እንባቸውን እያፈሰሱ
ወደ ሉሒት ወጡ፤
በሖሮናይም መንገድም፣
ስለ ጥፋታቸው ዋይ እያሉ ነጐዱ።
6 የኔምሬ ውሆች ደርቀዋል፤
ሣሩ ጠውልጎአል፤
ቡቃያውም ጠፍቶአል፤
ለምለም ነገር አይታይም።
7 ስለዚህ ያገኙትን ሀብት፣
ያከማቹትን ንብረት ከአኻያ ወንዝ ማዶ ተሸክመው ያሻግሩታል።
8 ጩኸታቸው እስከ ሞዓብ ዳርቻ ድረስ ያስተጋባል፤
ዋይታቸው እስከ ኤግላይም፣
ሰቈቃቸውም እስከ ብኤርኢሊም ደረሰ።
9 የዲሞንወንዞች በደም ተሞልተዋል፤
በዲሞን ላይ ግን ከዚያ ነገር የበለጠ አመጣለሁ፤
ከሞዓብ በሚሸሹት፣
በምድሪቱም ላይ በሚቀሩት አንበሳ እሰድዳለሁ።