1 ከምድረ በዳው ማዶ ካለችው ከሴላ፣
ለምድሪቱ ገዥ፣
ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ
የበግ ጠቦት ግብር ላኩ።
2 ከጐጆአቸው ተባርረው
ግራ እንደ ተጋቡ ወፎች፣
የሞዓብ ሴቶችም
በአርኖን ወንዝ መሻገሪያ እንዲሁ ይሆናሉ።
3 “ምክር ለግሱን፤
ውሳኔ ስጡን፤
በቀትር ጥላችሁን
እንደ ሌሊት አጥሉብን፤
የሸሹትን ደብቁ፤
ስደተኞችን አሳልፋችሁ አትስጡ።
4 የሞዓባውያን ስደተኞች ከእናንተ ጋር ይቈዩ፤
እናንተም ከአጥፊው መጠጊያ ሁኗቸው።”
የጨቋኙ ፍጻሜ ይመጣል፤
ጥፋቱ ያከትማል፤
እብሪተኛም ከምድር ገጽ ይጠፋል።
5 ዙፋን በፍቅር ይመሠረታል፤
ከዳዊት ቤትየሆነ፣
በፍርድ ፍትሕን የሚሻ፣
ጽድቅንም የሚያፋጥን፣
አንድ ሰው በታማኝነት በላዩ ይቀመጣል።
6 የሞዓብን መዘባነን፣
እጅግ መታበዩንና ኵራቱን፣
እብሪቱንና ስድነቱን ሰምተናል፤
ትምክህቱ ግን ከንቱ ነው።
7 ስለዚህ ሞዓባውያን ዋይ ይላሉ፤
በአንድነትም ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማሉ፤
ስለ ቂርሐራሴት ከተማ ሰዎች ትዝታ፣
በሐዘን ያለቅሳሉ።
8 የሐሴቦን ዕርሻ፣
የሴባማም የወይን ተክል ጠውልጎአል፤
የአሕዛብ ገዦች፣
ኢያዜርን ዐልፈው፣
ምድረ በዳውን ዘልቀው፣
ሥሮቻቸውን እስከ ባሕር ሰድደው የነበሩትን
የተመረጡ የወይን ተክሎችን
ረጋግጠዋል።
9 ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ተክል፣
ኢያዜር እንዳለቀሰች፣ እኔም አለቅሳለሁ፤
ሐሴቦን ሆይ፤ ኤልያሊ ሆይ፤
በእንባዬ አርስሻለሁ፤
ፍሬ ባፈራሽበት ወቅት የነበረው ሆታ፣
መከርሽም ሲደርስ የነበረው ደስታ ተቋርጦአልና።
10 ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤
በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤
እልልታም ቀርቶአል።
በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤
የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና።
11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጒርጒሮ ታሰማለች፤
አንጀቴም ስለ ቄርሔሬስ ታለቅሳለች፤
12 ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣
ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤
ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣
ዋጋ የለውም።
13 እግዚአብሔርአስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14 አሁን ግንእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የሞዓብ ክብርና የሕዝቧ ብዛት በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚቀረውም ሕዝብ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።”