ኢሳይያስ 19

ስለ ግብፅ የተነገረ ትንቢት

1 ስለ ግብፅ የተነገረ ንግር፤

እነሆ፤እግዚአብሔርበፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ

ወደ ግብፅ ይመጣል፤

የግብፅ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤

የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።

2 “ግብፃዊውን በግብፃዊው ላይ አስነሣለሁ፤

ወንድም ወንድሙን፣

ባልንጀራ ባልንጀራውን፣

ከተማም ከተማን፣

መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።

3 የግብፃውያን ልብ ይሰለባል፤

ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤

እነርሱም ጣዖታትንና የሙታንን መናፍስት፤

መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ምክር ይጠይቃሉ።

4 ግብፃውያንን አሳልፌ፣

ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤

አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል”

ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።

5 የዐባይ ወንዝ ይቀንሳል፤

ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።

6 መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤

የግብፅ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም።

ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤

7 እንዲሁም በዐባይ ዳር፣

በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ።

በዐባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣

በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።

8 ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤

በዐባይ ወንዝ ላይ መንጠቆአቸውን የሚወረውሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤

በውሃ ላይ መረባቸውን የሚጥሉ ሁሉ፣

ጒልበታቸው ይዝላል።

9 የተነደፈ የተልባ እግር የሚፈትሉ፣

የተባዘተ ጥጥ የሚሠሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቈርጣሉ።

10 ልብስ ሠሪዎች ያዝናሉ፤

ደመወዝተኞችም ልባቸው ይሰበራል።

11 የጣኔዎስ አለቆች በጣም ሞኞች ናቸው፤

የፈርዖን ጠቢባን ምክራቸው የማይረባ ነው፤

ፈርዖንን፣ “እኔ ከጥበበኞች አንዱ ነኝ፤

የጥንት ነገሥታትም ደቀ መዝሙር ነኝ”

እንዴት ትሉታላችሁ?

12 የእናንተ ጠቢባን አሁን የት አሉ?

የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር

በግብፅ ላይ ያሰበውን ነገር፣

እስቲ ያሳዩአችሁ፤ ያሳውቋችሁም።

13 የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤

የሜምፊስ ሹማምት ተታለዋል፤

የሕዝቧ ዋና ዋናዎች፣

ግብፅን አስተዋታል።

14 እግዚአብሔርየድንዛዜን መንፈስ አፍሶባቸዋል፤

ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ፣

ግብፅንም በምታደርገው ነገር ሁሉ

እንድትንገዳገድ አደረጓት።

15 ራስም ይሁን ጅራት፣ የዘንባባ ዝንጣፊም ይሁን ደንገል፣

ለግብፅ የሚያደርጉላት አንዳች ነገር የለም።

16 በዚያን ቀን ግብፃውያን እንደ ሴት ይሆናሉ፤ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርበእነርሱ ላይ ካነሣው ክንዱ የተነሣ በፍርሀት ይንቀጠቀጣሉ።

17 የይሁዳ ምድር በግብፅ ላይ ሽብር ትነዛለች፤ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርበእነርሱ ላይ ካቀደው የተነሣ፣ ስለ ይሁዳ፣ ወሬ የሰማ ሁሉ ይሸበራል።

18 በዚያ ቀን አምስት የግብፅ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ የሰራዊት ጌታየእግዚአብሔርምወገን ለመሆን ቃል ኪዳን ይገባሉ፤ ከእነዚህም ከተሞች አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።

19 በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከልለእግዚአብሔርመሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይለእግዚአብሔርዐምድ ይቆማል።

20 ይህም በግብፅ ምድር ለሰራዊት ጌታለእግዚአብሔርምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨን ቋቸውም የተነሣ ወደእግዚአብሔርሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል።

21 እግዚአብሔርራሱን ለግብፃውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀንእግዚአብሔርንያውቁታል፤ በመሥዋዕትና በእህል ቍርባንም ያመልኩታል።ለእግዚአብሔርስለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል።

22 እግዚአብሔርግብፅን በመቅሠፍት ይመታታል፤ መትቶም፤ ይፈውሳቸዋል። እነርሱም ወደእግዚአብሔርይመለሳሉ፤ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።

23 በዚያ ቀን ከግብፅ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብፅ፣ ግብፃውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብፃውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ።

24 በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብፅና ከአሦር ጋር የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች።

25 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብፅ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *