ኢሳይያስ 2

የእግዚአብሔር ተራራ

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ይህ ነው፤

2 በዘመኑም ፍጻሜ፣

የእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ተራራ

ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤

ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤

ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።

3 ብዙ ሕዝቦችም መጥተው እንዲህ ይላሉ፤

“ኑ፤ ወደእግዚአብሔርተራራ፣

ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤

እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤

በጐዳናውም እንሄዳለን።”

ሕግ ከጽዮን፣

የእግዚአብሔርቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።

4 እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤

የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል።

እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ

ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ።

ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤

ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።

5 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ ኑ፤

በእግዚአብሔርብርሃን እንመላለስ።

የእግዚአብሔር ቀን

6 የያዕቆብ ቤት የሆነውን፣

ሕዝብህን ትተሃል፤

እነርሱ በምሥራቅ ሰዎች ከንቱ አምልኮ ተሞልተዋልና፤

እንደ ፍልስጥኤማውያን ያሟርታሉ፤

ከባዕዳን ጋር አገና ይማታሉ።

7 ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤

ሀብታቸውም ልክ የለውም።

ምድራቸው በፈረሶች ተሞልታለች፤

የሠረገሎቻቸውም ብዛት ልክ የለውም።

8 ምድራቸው በጣዖታት ተሞልታለች፤

ጣቶቻቸው ላበጇቸው፣

ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ።

9 ሰው ዝቅ ብሎአል፤

የሰው ልጅም ተዋርዶአል፤

ስለዚህ በደላቸውን ይቅር አትበል።

10 ከእግዚአብሔርአስፈሪነት ከግርማው ሽሽ፤

ወደ ዐለቶች ሂድ፤

በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።

11 የእብሪተኛ ሰው ዐይን ይሰበራል፤

የሰዎችም ትዕቢት ይዋረዳል፤

በዚያን ቀንእግዚአብሔርብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።

12 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር

እብሪተኛውንና ትዕቢተኛውን ሁሉ፣

የተኵራራውን በሙሉ

የሚያዋርድበት ቀን አለው።

13 ረዥምና ከፍ ከፍ ያሉትን የሊባኖስ ዝግባዎች ሁሉ፣

የባሳንን የወርካ ዛፎች ሁሉ፣

14 ታላላቁን ተራራ ሁሉ፣

ከፍ ያለው ኰረብታ ሁሉ፣

15 ረጃጅሙን ግንብ ሁሉ፣

የተመሸገውን ቅጥር ሁሉ፣

16 የተርሴስን መርከቦችሁሉ፣

የክብር ጀልባዎችን ሁሉ የሚያዋርድበት ቀን አለው።

17 የሰው እብሪት ይዋረዳል፤

የሰውም ኵራት ይወድቃል፤

በዚያን ቀንእግዚአብሔርብቻ ከፍ ከፍ ይላል፤

18 ጣዖቶች ሁሉ ፈጽሞ ይወድማሉ።

19 እግዚአብሔርምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣

ሰዎች ከአስፈሪነቱ

ከግርማውም የተነሣ፣

ወደ ዐለት ዋሻ

ወደ መሬትም ጒድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ።

20 በዚያን ቀን ሰዎች

ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፣

የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን

ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ።

21 እግዚአብሔርምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣

ሰዎች ከአስፈሪነቱ

እንዲሁም ከግርማው የተነሣ፣

ወደ ድንጋይ ዋሻ፣

ወደ ዐለት ስንጣቂ ሮጠው ይገባሉ።

22 እስትንፋስ አፍንጫው ላይ ባለች

በሰው አትታመኑ፤

ከቶ ምን የሚበጅ ነገር አለው!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *