ወዮ ለኤፍሬም
1 ለኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል ለሆነች፣
በለመለመ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣
የክብሩ ውበት ለሆነች ጠውላጋ አበባ፣
የወይን ጠጅ ለዘራቸው መኵራሪያ ለሆነች፣
ለዚያች ከተማ ወዮላት!
2 እነሆ፤ ጌታ ኀያልና ብርቱ የሆነ ነገር አለው፤
ይህም እንደ በረዶ ወጀብ፣ እንደሚያጠፋ ዐውሎ ነፋስ፣
እንደ ኀይለኛ ማዕበል፣ እንደ ከባድ ዝናብ፣
በኀይል ወደ ምድር ይጥላታል።
3 የኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል፣
በእግር ይረገጣል።
4 በለምለሙ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣
የክብሩ ውበት የሆነች ጠውላጋ አበባ፣
ከመከር በፊት እንደ ደረሰች፣
ሰውም ድንገት አይቶ እንደሚቀጥፋት
ወዲያውኑም እንደሚውጣት በለስ ትሆናለች።
5 በዚያን ቀን የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣
ለተረፈው ሕዝቡ፣
የክብር ዘውድ፣
የውበትም አክሊል ይሆናል።
6 እርሱም በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጠው፣
የፍትሕ መንፈስ፣
ጦርን ከከተማዪቱ በር ላይ ለሚመልሱም፣
የኀይል ምንጭ ይሆናል።
7 እነዚህም በወይን ጠጅ ይንገዳገዳሉ፤
በሚያሰክርም መጠጥ ይወላገዳሉ፤
ካህናቱና ነቢያቱ በሚያሰክር መጠጥ ተንገደገዱ፤
በወይን ጠጅ ነገር ተምታታባቸው፤
በሚያሰክር መጠጥ ተወላገዱ፤
ራእይ ሲያዩ ይስታሉ፤
ፍርድ ሲሰጡም ይሰናከላሉ።
8 የማእድ ገበታቸው ሁሉ በትፋት ተሞልቶአል፤
ከትውኪያም የጸዳ ቦታ የለም።
9 እነርሱም እንዲህ ይላሉ፤ “የሚያስተምረው ማንን ነው?
መልእክቱን የሚያብራራውስ ለማን ነው?
ወተት ለተዉት ሕፃናት?
ወይስጡት ለጣሉት?
10 በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ
ትእዛዝ፤
በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤
እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት ነውና።
11 እንግዲያማእግዚአብሔር፣
በባዕድ ልሳን በእንግዳ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል።
12 እርሱ፣
“ይህቺ የዕረፍት ቦታ ናት፤ የደከመው ይረፍ፤
ይህቺ የእፎይታ ቦታ ናት” ያለው ለማን ነበር?
እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።
13 ስለዚህየእግዚአብሔርቃል፣
በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤
በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤
እዚህ ጥቂት እዚያ ጥቂት ይሆንባቸዋል።
ይህ የሚሆንባቸው ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፣
እንዲቈስሉና በወጥመድ እንዲያዙ፣
እንዲማረኩም ነው።
14 ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ፣
እናንት ፌዘኞችየእግዚአብሔርንቃል ስሙ።
15 እናንት፣ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤
ከሲኦልም ጋር ስምምነት አድርገናል፤
ውሸትን መጠጊያችን፣
ሐሰትንመደበቂያችን አድርገናል፤
ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣
ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል።
16 ስለዚህ ልዑልእግዚእብሔርእንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣
ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣
በጽዮን አስቀምጣለሁ፤
በእርሱም የሚያምን አያፍርም።
17 ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣
ጽድቅንም ቱንቢ አደርጋለሁ፤
ውሸት መጠጊያችሁን የበረዶ ዝናብ ይጠራርገዋል
መደበቂያችሁንም ውሃ ያጥለቀልቀዋል።
18 ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይሻራል፤
ከሲኦልም ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት ይፈርሳል፤
ታላቁ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣
እናንተም ትጠራረጋላችሁ።
19 በመጣ ቍጥር ይዞአችሁ ይሄዳል፤
ማለዳ ማለዳ፣ በቀንና በሌሊትም
ይጠራርጋል።”
ይህን ቃል ብታስተውሉ፣
ሽብር በሽብር በሆነ ነበር።
20 እግር ዘርግቶ እንዳይተኛ ዐልጋው አጭር ነው፤
ሰውነትንም ለመሸፋፈን ብርድ ልብሱ ጠባብ ነው።
21 እግዚአብሔርሥራውን፣ አዎን ድንቅ ሥራውን ሊሠራ፣
ተግባሩን፣ እንግዳ የሆነ ተግባሩን ሊያከናውን፣
በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው ይነሣል፣
በገባዖን ሸለቆ እንዳደረገው ይነሣሣል።
22 እንግዲህ ፌዛችሁን አቁሙ፤
አለዚያ እስራታችሁ ይጸናባችኋል፤
ጌታ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣
መላውን ምድር ለማጥፋት ያወጀውን ዐዋጅ ሰምቻለሁ።
23 አድምጡ ድምፄን ስሙ፤
አስተውሉ ቃሌንም ስሙ።
24 ገበሬ ሊዘራ መሬቱን ሲያዘጋጅ ያለ ማቋረጥ ያርሳልን?
ጓሉን ሲከሰክስ፣ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማልን?
25 ዕርሻውን አስተካክሎ፣
ጥቍር አዝሙድና ከሙን አይዘራምን?
ስንዴውንስ በትልሙ፣
ገብሱን በተገቢ ቦታው፣
አጃውንም በተመደበው ስፍራ አይዘራምን?
26 አምላኩ ያስተምረዋል፤
ትክክለኛውንም መንገድ ያሳየዋል።
27 ጥቍር አዝሙድ በመውቂያ መሣሪያ አይወቃም፤
ከሙን የሠረገላ መንኰራኵር አይሄድበትም፤
ጥቍር አዝሙድ በበትር፣
ከሙንም በዘንግ ይወቃል።
28 እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤
ስለዚህ አንድ ሰው ለዘላለም እህል ሲወቃ አይኖርም።
የመውቂያውን መንኰራኵር ቢያኼድበትም፣
ፈረሶቹ አይደፈጥጡትም።
29 ይህ ሁሉ የሚሆነው በምክሩ ድንቅ በጥበቡ
ታላቅ ከሆነው፣
ከሰራዊት ጌታከእግዚአብሔርዘንድ ነው።