ወዮ ለዳዊት ከተማ
1 ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ፣
አርኤል፣ አርኤል ወዮል
ዓመት በዓመት ላይ ጨምሪ፣
ዐውደ ዓመትሽም ይቀጥል።
2 ነገር ግን አርኤልንእከባለሁ፤
ታለቅሳለች፤ ዋይ ዋይ ትላለች፤
ለእኔም እንደ መሠዊያ ስፍራ ትሆንልኛለች።
3 በዙሪያሽ እሰፍራለሁ፤
በቅጥር እከብሻለሁ፤
የከበባ ዐምባም ሠርቼ አስጨንቅሻለሁ።
4 ወደ ታች ትወርጃለሽ፤ ከምድርም በታች ትናገሪያለሽ፤
ንግግርሽ ከትቢያ እየተጒተመተመ ይወጣል፤
ድምፅሽ እንደ መናፍስት ድምፅ ከመሬት ወደ ላይ ይመጣል፤
ንግግርሽ ከትቢያ ያንሾካሹካል።
5 ነገር ግን ብዙ ጠላቶችሽ እንደ ትቢያ ብናኝ፣
መንጋ ጨካኞችም በነፋስ እንደሚነጻ
ገለባ ይሆናሉ።
ድንገት ሳይታሰብም፣
6 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣
በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣
በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል።
7 አርኤልን የሚወጋ የአሕዛብ ሁሉ መንጋ፣
በእርሷና በምሽጓ ላይ አደጋ የሚጥልና የሚከባት፣
እንደ ሕልም
በሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናል።
8 የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ፣
ነገር ግን ሲነቃ ራቡ እንዳልለቀቀው፣
የጠማውም ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ፣
ነገር ግን ሲነቃ እንደ ዛለና ጥማቱም እንዳልተወው፣
የጽዮንን ተራራ የሚወጋ፣
የአሕዛብ መንጋ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።
9 ነሁሉሉ፤ ተደነቁም፤
ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤
በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤
በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።
10 እግዚአብሔርከባድ እንቅልፍ ጥሎባችኋል፤
ዐይኖቻችሁን፣ ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤
ራሶቻችሁን፣ ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።
11 ይህ ሁሉ ራእይ በጥቅልል መጽሐፍ ውስጥ እንደ ታሸገ ቃል ሆኖባችኋል። ጥቅልሉንም መጽሐፍ ማንበብ ለሚችል ሰው፣ “እባክህ አንብልን” ብላችሁ ብትሰጡት፣ “ታሽጓልና አልችልም” ይላችኋል።
12 ደግሞም ጥቅልሉን መጽሐፍ ማንበብ ለማይችል ሰው፣ “እባክህን አንብልን” ብላችሁ ብትሰጡ፣ “ማንበብ አልችልም” ይላችኋል።
13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤
በከንፈሩም ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
የሚያመልከኝም፣
ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው።
14 ስለዚህ ይህን ሕዝብ በድንቅ ላይ ድንቅ
ነገር እያደረግሁ፣
ዳግመኛ አስገርመዋለሁ፤
የጥበበኞች ጥበብ ይጠፋል፤
የአስተዋዮችም ማስተዋል ይበናል።”
15 ሐሳባቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ፣
ወደ ጥልቅ ጒድጓድ ለሚወርዱ
ሥራቸውንም በጨለማ ለሚያከናውኑ፣
“ማን ያየናል? ማንስ ያውቅብናል” ለሚሉ ወዮላቸው!
16 እናንተ ነገሮችን ትገለብጣላችሁ
ሸክላ ሠሪውን እንደ ሸክላ ትመለከታላችሁ፤
ለመሆኑ፣ ተሠሪ ሠሪውን፣
“እርሱ አልሠራኝም” ይለዋልን?
ሸክላ የሠራውን፣
“እርሱ ምንም አያውቅም” ይለዋልን?
17 ሊባኖስ ወደ ለም ዕርሻነት ለመለወጥ፣
ለም የሆነውም መሬት ወደ ዱርነት ለመለወጥ ጥቂት ጊዜ አልቀረውምን?
18 በዚያን ጊዜ ደንቈሮ የጥቅልሉን መጽሐፍ ቃል ይሰማል፤
የዐይነ ስውሩም ዐይኖች
ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ።
19 ትሑታንበእግዚአብሔር፣
ምስኪኖችም በእስራኤል ቅዱስ እንደ ገና ሐሤት ያደርጋሉ።
20 ጨካኞች እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤
ፌዘኞችም በነው ይጠፋሉ፤
ለክፋት ያደፈጡ ሁሉ ይወገዳሉ።
21 ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፣
በተከሳሽ ላይ ወጥመድ የሚዘረጉ፣
በሐሰት ምስክር ፍትሕን ከንጹሓን የሚቀሙ ይቈረጣሉ።
22 ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠውእግዚአብሔር
ለያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፤
“ያዕቆብ ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም፤
ፊቱም ከእንግዲህ አይለዋወጥም።
23 በመካከላቸው የእጄ ሥራ የሆኑ፣
ልጆቻቸውን ሲያዩ፣
ስሜን ይቀድሳሉ፤
የያዕቆብን ቅዱስ ቅድስና ያውቃሉ፤
በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሀት ይቆማሉ።
24 በመንፈስ የሳቱ ያስተውላሉ፤
የሚያጒረመርሙም ምክር ይቀበላሉ።”