በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የሚመጣ ፍርድ
1 እነሆ፤ ጌታ፣
የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር
ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ
ድጋፉንና ርዳታውን፣
የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤
2 ጀግናውንና ተዋጊውን፣
ፈራጁንና ነቢዩን፣
አስማተኛውንና ሽማግሌውን፣
3 የአምሳ አለቃውንና ባለ ማዕረጉን፣
አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለ ሙያ፣
ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል።
4 ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤
ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል።
5 ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤
ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፣
ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፣
ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል።
6 ሰውም በአባቱ ቤት
ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፣
“አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤
ይህንንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ” ይለዋል።
7 እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣
“እኔ መፍትሔ አልሆንም፤
በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤
የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል።
8 ኢየሩሳሌም ተንገዳግዳለች፤
ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤
ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸውእግዚአብሔርንየሚቃወም፣
የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና።
9 የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤
ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤
አይደብቁትምም፤
ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ።
ወዮላቸው!
10 ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤
የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና።
11 በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት
ይመጣባቸዋል፤
የእጃቸውን ያገኛሉና።
12 ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤
ሴቶችም ይገዟቸዋል።
ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤
ከመንገድህም መልሰውሃል።
13 እግዚአብሔርበፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦአል፤
በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቶአል።
14 እግዚአብሔር፣
ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤
“የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤
ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤
15 ሕዝቤን በችግር ስታደቁት፣
የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?”
ይላል ጌታ፣
የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።
16 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤
ዐንገታቸውን እያሰገጉ፣
በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤
እየተቈነኑ በመራመድ፣
የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ።
17 ስለዚህ፣ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ
ቈረቈር ያመጣል፤
እግዚአብሔርምራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል።
18 በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፣ የጠጒር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፣
19 የጆሮ ጒትቻውን፣ የእጅ አንባሩን፣ የፊት መሸፈኛውን፣
20 የራስ መሸፈኛውን፣ ዐልቦውን፣ ሻሹን፣ የሽቶ ብልቃጡን፣ አሸንክታቡን፣
21 የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፣
22 ያማረውን ቀሚስ፣ የውስጥ ልብሱን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣
23 መስታወቱን፣ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፣ የራስ ጌጡን፣ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል።
24 በሽቶ ፈንታ ግማት፣
በሻሽ ፈንታ ገመድ፣
አምሮ በተሠራ ጠጒር ፈንታ ቡሀነት፣
ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፣
በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል።
25 ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፣
ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ።
26 የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤
እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።