ኢሳይያስ 31

በግብጽ ለሚደገፉ ወዮውላቸው

1 ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣

ከእግዚአብሔርምርዳታን ለማይሹ፣

ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፣

በፈረሶች ለሚታመኑ፣

በሠረገሎቻቸው ብዛት፣

በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!

2 እርሱም ግን ጠቢብ ነው፤ ጥፋትን ያመጣል፤

ቃሉን አያጥፍም።

በክፉ አድራጊዎች ቤት ላይ፣

በደለኞችንም በሚረዱ ላይ ይነሣል።

3 ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤

ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤

እግዚአብሔርእጁን ሲዘረጋ፣

ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤

ተረጂውም ይወድቃል፤

ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።

4 እግዚአብሔርእንዲህ ብሎኛል፤

“አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል

የሰበረውን ይዞ ሲያገሣ፣

ብዙ እረኞች

ተጠራርተው ሲመጡበት፣

ጩኸታቸው እንደማያስፈራው፣

በድምፃቸውም እንደማይታወክ፣

የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣

በጽዮን ተራራና በከፍታዎቿ ላይ ለውጊያ እንዲሁ ይወርዳል።

5 በዐናት ላይ እንደሚያንዣብቡ ወፎች፣

የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርኢየሩሳሌምን እንዲሁ ይጋርዳታል፤

ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤

በላይዋ ያልፋል፤ ያድናታልም።”

6 እናንተ እስራኤላውያን ሆይ፤ እጅግ ወዳ መፃችሁበት ወደ እርሱ ተመለሱ።

7 በዚያን ቀን በኀጢአት የተሞላ እጃችሁ የሠራቸውን የወርቅና የብር ጣዖቶች ሁላችሁም ትጥላላችሁና።

8 “አሦር የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፤

የሥጋ ለባሽ ያልሆነም ሰይፍ ይበላዋል።

ከሰይፍ ፊት ይሸሻል፤

ጐልማሶቹም የግዳጅ ሥራ ይሠራሉ።

9 ጠንካራ ምሽጉ በሽብር ምክንያት ይወድቃል፤

መሪዎቹም የጦር ዐርማ ሲያዩ

በድንጋጤ ይዋጣሉ”

ይላል እሳቱ በጽዮን፣

ማንደጃውም በኢየሩሳሌም የሆነእግዚአብሔር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *