የኢየሩሳሌም ዐርነት ታወጀ
1 ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ገባ።
2 የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ኤልያቄምንና ጸሓፊውን ሳምናስን እንዲሁም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ሁሉም ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው።
3 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ሕፃናት ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኖአል።
4 ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃልእግዚአብሔርአምላክህ ይሰማ ይሆናል፤እግዚአብሔርአምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።”
5 የንጉሡ የሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤
6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤‘እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር።
7 እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”
8 የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቆ መሄዱን ሲሰማ፣ ከነበረበት ተመለሰ፤ ንጉሡም የልብናን ከተማ ሲወጋ አገኘው።
9 ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤
10 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልህ።
11 እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?
12 የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን?
13 የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”
የሕዝቅያስ ጸሎት
14 ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውንበእግዚአብሔርፊት ዘረጋው።
15 ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደእግዚአብሔርጸለየ፤
16 “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።
17 አቤቱ፣እግዚአብሔርሆይ፤ ጆሮህን አዘንብል፤ አድምጥም።እግዚአብሔርሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈት፤ ተመልከትም። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።
18 “እግዚአብሔርሆይ፤ በርግጥ የአሦር ነገሥታት እነዚህን ሕዝቦች፣ ምድራቸውንም ሁሉ ባድማ አድርገዋል።
19 አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና።
20 አሁንም፣እግዚአብሔርአምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተእግዚአብሔርብቻ አምላክ እንደሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”
የሰናክሬም ውድቀት
21 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣
22 እግዚአብሔርበእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤
“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣
ንቃሃለች፣ አፊዛብሃለች፤
የኢየሩሳሌም ልጅ፣
አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።
23 የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?
ድምፅህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፣
ዐይንህን በትዕቢት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?
በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እኮ!
24 በመልእክተኞችህ በኩል፣
በጌታ ላይ ብዙ የስድብ ቃል ተናገርህ፤
እንዲህም አልህ፤
“በሰረገሎቼ ብዛት፣
የተራሮችንም ከፍታ፣
የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤
ረጃጅም ዝግባዎችን፣
የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤
እጅግ ወደራቁት ከፍታዎች፣
እጅግ ውብ ወደ ሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ፤
25 በባዕድ ምድርጒድጓዶችን ቈፈርሁ፤
ከዚያም ውሃ ጠጣሁ።
የግብፅን ምንጮች ሁሉ፣
በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።”
26 “ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣
ጥንትም እንዳቀድሁት፣
አልሰማህምን?
አሁን ደግሞ እንዲፈጸም አደረግሁት፤
አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የድንጋይ
ክምር አደረግሃቸው።
27 የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጦአል፤
ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤
በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣
እንደ ለጋ ቡቃያ፣
በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣
በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።
28 “ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣
መምጣት መሄድህ ምን ጊዜ እንደሆነ፣
በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደም ትነሣሣ ዐውቃለሁ።
29 በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣
እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣
በአፍንጫህ ስናጌን፣
በአፍህ ልጓሜን አገባለሁ፤
በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ
አደርግሃለሁ።’
30 “ሕዝቅያስ ሆይ፤ ይህ ምልክት ይሆንልሃል፤
“በዚህ ዓመት የገቦውን፣
በሚቀጥለው ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤
በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤
ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።
31 እንደ ገናም የይሁዳ ቤት ቅሬታ፣
ሥሩን ወደ ታች ይሰዳል፤ ከላይም ፍሬ ያፈራል፤
32 ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣
የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና፤
የሰራዊት ጌታየእግዚአብሔርቅናት
ይህን ያደርጋል።
33 “ስለዚህእግዚአብሔርስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤
“ወደዚች ከተማ አይገባም፤
ፍላጻ አይወረውርባትም፤
ጋሻ አንግቦ አይመጣባትም፤
በዐፈር ቍልልም አይከባትም።
34 በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤
ወደዚች ከተማም አይገባም”
ይላልእግዚአብሔር።
35 “ስለ ራሴና፣ ስለ አገልጋዬም ስለ ዳዊት፣
ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።”
36 ከዚያምየእግዚአብሔርመልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ፤ በሰፈር ያሉት ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር።
37 ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም አመለጠ፤ ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ።
38 ሰናክሬም በአምላኩ በናሳራክ ቤተ ጣዖት በሚሰግድበት ጊዜ፣ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም ወደ አራራት ምድር ኰበለሉ፤ ልጁም አስራዶን በምትኩ ነገሠ።