ኢሳይያስ 38

የሕዝቅያስ መታመም

1 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታመመ፤ ሞት አፋፍ ደረሰ፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣“እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አሰናዳ’ ” አለው።

2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ እንዲህ ሲል ወደእግዚአብሔርጸለየ፤

3 “እግዚአብሔርሆይ፤ በፊትህ በታማኝነትና በፍጹም ልብ ደስ የሚያሰኝህንም በማድረግ እንዴት እንደኖርሁ አቤቱ አስብ።” ሕዝቅያስም አምርሮ አለቀሰ።

4 የእግዚአብሔርምቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

5 “ሂድና ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ።

6 አንተንና ይህቺን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ለከተማዋም እከላከልላታለሁ።

7 “ ‘እግዚአብሔርየገባልህን ቃል እንደሚፈጽምልህ፣የእግዚአብሔርምልክት ይህ ነው፤

8 በአካዝ የሰዓት መቍጠሪያ ደረጃ ላይ፣ የወረደውን የፀሓይ ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።’ ” ስለዚህ ወርዶ የነበረው የፀሓይ ጥላ ያንኑ ያህል ወደ ኋላ ተመለሰ።

9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከተፈወሰ በኋላ የጻፈው ጽሕፈት፤

10 እኔ፣ “በዕድሜዬ እኩሌታ፣

በሲኦል ደጆች ማለፍ አለብኝን?

የቀረውንስ ዘመኔን ልነጠቅ ይገባልን?” አልሁ።

11 እንዲህም አልሁ፤ “ዳግምእግዚአብሔርን፣

እግዚአብሔርንበሕያዋን ምድር አላይም፤

ከእንግዲህም የሰውን ዘር አላይም፤

በዚህ ዓለም ከሚኖሩትም ጋር አልሆንም።

12 ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤

ከእኔም ተወሰደ፤

ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤

ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤

ከጠዋት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

13 እስከ ማለዳ በትዕግሥት ጠበቅሁ፤

እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ሰባበረ፤

ከጠዋት እስከ ማታም ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

14 እንደ ጨረባ፣ እንደ ሽመላም ተንጫጫሁ፤

እንደ ርግብ አልጐመጐምሁ፤

ዐይኖቼ ወደ ሰማይ በመመልከት ደከሙ፤

ጌታ ሆይ፤ ተጨንቄአለሁና ታደገኝ።”

15 እንግዲህ ምን እላለሁ?

እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱ ደግሞ ይህን አድርጓል፤

ስለ ነፍሴ ጭንቀት፣

ዕድሜዬን ሁሉ በትሕትና እሄዳለሁ።

16 ጌታ ሆይ፤ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ይኖራሉ፤

መንፈሴም እንዲሁ በእነዚህ ሕይወትን ያገኛል፤

ፈወስኸኝ፤

በሕይወትም አኖርኸኝ።

17 እነሆ፤ በሥቃይ የተጨነቅሁት፣

ለጥቅሜ ሆነ፤

ከጥፋት ጒድጓድ፣

በፍቅርህ ጠበቅኸኝ፤

ኀጢአቴንም ሁሉ፣

ወደ ኋላህ ጣልኽ።

18 ሲኦል አያመሰግንህም፤

ሞት አያወድስህም፤

ወደ ጒድጓድ የሚወርዱ፣

የአንተን ታማኝነት ተስፋ አያደርጉም።

19 እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣

ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል።

ስለ አንተ ታማኝነትም፣

አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።

20 እግዚአብሔርያድነኛል፤

ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ሁሉ፣

በእግዚአብሔርቤተ መቅደስ፣

አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።

21 ኢሳይያስም፣ “የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳችሁ በዕባጩ ላይ አድርጉለት እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር።

22 ሕዝቅያስም፣ “ወደእግዚአብሔርቤተ መቅደስ እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *