ኢሳይያስ 40

የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያጽናና ቃል

1 አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤

ይላል አምላካችሁ።

2 ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤

ዐውጁላትም፤

በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቶአል፤

የኀጢአቷም ዋጋ ተከፍሎአል፤

ስለ ኀጢአቷ ሁሉከእግዚአብሔርእጅ

ሁለት ዕጥፍ ተቀብላለች።

3 የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤

“የእግዚአብሔርንመንገድ፣

በምድረ በዳ አዘጋጁ፤

ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣

በበረሓ አስተካክሉ።

4 ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፤

ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤

ወጣ ገባው ምድር ይስተካከላል፤

ሰርጓጒጡም ሜዳ ይሆናል።

5 የእግዚአብሔርምክብር ይገለጣል፤

ሰው ሁሉ በአንድነት ያየዋል፤

የእግዚአብሔርአፍ ይህን ተናግሮአልና።”

6 ድምፅም፣ “ጩኽ” አለኝ፤

እኔም፣ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ።

“ሰው ሁሉ እንደ ሣር ነው፤

ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።

7 ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤

የእግዚአብሔርእስትንፋስ ነፍሶበታልና፤

ሕዝቡ በርግጥ ሣር ነው።

8 ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤

የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

9 አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤

ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤

አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣

ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጩኽ።

ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤

ለይሁዳም ከተሞች፣

“እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።

10 እነሆ፤ ልዑልእግዚአብሔርበኀይል

ይመጣል፤

ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል።

እነሆ፤ ዋጋው ከእርሱ ጋር ነው፤

የሚከፍለውም ብድራት አብሮት አለ።

11 መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤

ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤

በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤

የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።

12 ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣

ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣

የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣

ተራሮችን በሚዛን፣

ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ ማነው?

13 የእግዚአብሔርንመንፈስ የተረዳ፣

አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማነው?

14 ዕውቀት ለማግኘትእግዚአብሔርማንን አማከረ?

ትክክለኛውንስ መንገድ ማን አስተማረው?

ዕውቀትን ያስተማረው፣

የማስተዋልንም መንገድ ያሳየው ማን ነበር?

15 እነሆ፤ አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤

በሚዛን ላይ እንዳለ ትቢያ ይቈጠራሉ፤

ደሴቶችንም እንደ ደቃቅ ዐፈር ይመዝናቸዋል።

16 ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤

የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።

17 አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤

ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።

18 እንግዲህ፣እግዚአብሔርንከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ?

ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?

19 የተቀረጸውንማ ምስል ባለጅ ይቀርጸዋል፤

ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤

የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።

20 እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣

የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤

የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣

ታዋቂ ባለ ሙያ ይፈልጋል።

21 አላወቃችሁምን?

አልሰማችሁምን?

ከጥንት አልተነገራችሁምን?

ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

22 እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤

ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው።

ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤

እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።

23 አለቆችን ኢምንት፣

የዚህን ዓለም ገዦች እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል።

24 ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣

ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣

ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩ

አነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤

ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው።

25 ቅዱሱ፣ “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ?

የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።

26 ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤

እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው?

የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣

በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው።

ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣

አንዳቸውም አይጠፉም።

27 ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ?

እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ?

“መንገዴከእግዚአብሔርተሰውራለች፤

ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ?

28 አታውቅምን?

አልሰማህምን?

እግዚአብሔርየዘላለም አምላክ፣

የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው።

አይደክምም፤ አይታክትም፤

ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።

29 ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤

ለዛለው ጒልበት ይጨምራል።

30 ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤

ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ።

31 እግዚአብሔርንተስፋ የሚያደርጉ ግን፣

ኀይላቸውን ያድሳሉ፤

እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤

ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤

ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *