የእስራኤል ረዳት
1 “ደሴቶች ሆይ፤ በፊቴ ዝም በሉ፤
አሕዛብ ኀይላቸውን ያድሱ፤
ቀርበው ይናገሩ፤
በፍርድም ፊት እንገናኝ።
2 “ከምሥራቅ አንዱን ያነሣው፣
በጽድቅም ወደ አገልግሎቱ የጠራው ማን ነው?
አሕዛብን አሳልፎ ሰጠው፤
ነገሥታትን በፊቱ አስገዛለት
በሰይፉም እንደ ትቢያ አቦነናቸው፤
በቀስቱም በነፋስ እንደ ተበተነ ገለባ አደረጋቸው።
3 አሳደዳቸው ያለ ችግር ዐልፎ ሄደ፤
እግሩም ቀድሞ ባልረገጠው መንገድ ተጓዘ።
4 ይህን የሠራና ያደረገ፣
ትውልድን ከጥንት የጠራ ማን ነው?
እኔእግዚአብሔርከፊተኛው፣
ከኋለኛውም ጋር፤ እኔው ነኝ።”
5 ደሴቶች አይተው ፈሩ፤
የምድር ዳርቾች ደነገጡ፤
ቀረቡ፤ ወደ ፊትም መጡ።
6 እያንዳንዱ ይረዳዳል፤
ወንድሙንም፣ “አይዞህ” ይለዋል።
7 ባለጅ የወርቅ አንጥረኛውን ያበረታታዋል፤
በመዶሻ የሚያሳሳውም፣
በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያነቃቃዋል፤
ስለ ብየዳም ሥራው፣ “መልካም ነው” ይለዋል፤
የጣዖቱ ምስል እንዳይወድቅም በምስማር ያጣብቀዋል።
8 “አንተ ግን፣ ባሪያዬ እስራኤል፣
የመረጥሁ ያዕቆብ፣
የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፤
9 ከምድር ዳርቻ ያመጣሁህ፣
ከአጥናፍም የጠራሁህ፣
‘አንተ ባሪያዬ ነህ’ ያልሁህ፤
መረጥሁህ እንጂ፤ አልጣልሁህም።
10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤
አምላክህ ነኝና አትደንግጥ።
አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤
በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
11 “እነሆ፤ የተቈጡህ ሁሉ፣
እጅግ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፤
የሚቋቋሙህ፣
እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።
12 ጠላቶችህን ብትፈልጋቸው እንኳ፣
አታገኛቸውም፤
የሚዋጉህም፣
እንዳልነበሩ ይሆናሉ።
13 እኔእግዚአብሔርአምላክህ ‘አትፍራ፤
እረዳሃለሁ’
ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና።
14 አንት ትል ያዕቆብ፣
ታናሽ እስራኤል ሆይ፤
‘አትፍራ እኔ እረዳሃለሁ’ ” ይላልእግዚአብሔር፤
የሚቤዥህ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
15 “እነሆ፣ አዲስ
የተሳለና ብዙ ጥርስ ያለው ማሄጃ አደርግሃለሁ፤
ተራሮችን ታሄዳለህ፤ ታደቃቸዋለህ፤
ኰረብቶችንም ገለባ ታደርጋቸዋለህ።
16 ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤
ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል።
አንተ ግንበእግዚአብሔርደስ ይልሃል፤
በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ።
17 “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤
ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤
ጒሮሮአቸው በውሃ ጥም ደርቆአል።
ነገር ግን እኔእግዚአብሔርእመልስላቸዋለሁ፤
እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።
18 በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣
በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮች አፈልቃለሁ።
ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣
የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።
19 በምድረ በዳ፣
ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤
በበረሃ፣ ጥድን፣ አስታንና
ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ።
20 ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤
የእግዚአብሔርእጅ ይህን እንዳደረገ፣
የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣
በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።
21 “ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ” ይላልእግዚአብሔር፤
“ማስረጃችሁን አምጡ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።
22 “የሚሆነውን እንዲነግሩን፣
ጣዖቶቻችሁን አምጡ፤
እንድንገነዘብ፣
ፍጻሜአቸውን እንድናውቅ፣
የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ነበሩ ንገሩን፤
ስለሚመጡትም ነገሮች ግለጹልን።
23 እናንት አማልክት መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ፣
ወደ ፊት ስለሚሆነው ንገሩን፤
እንድንደነግጥ፣ በፍርሀት እንድንዋጥ፣
መልካምም ሆነ ክፉ፣ አንድ ነገር አድርጉ።
24 እነሆ፤ እናንት ከምንም የማትቈጠሩ ናችሁ፤
ሥራችሁ ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው፤
የመረጣችሁም አስጸያፊ ነው።
25 “አንዱን ከሰሜን አስነሣሁት፤ እርሱም ይመጣል፤
ከፀሓይ መውጫ የሚመጣው፣ ስሜን የሚጠራ ነው፤
ሸክላ ሠሪ ዐፈር እንደሚረግጥ፣
አለቆችን እንዲሁ እንደ ጭቃ ይረግጣል።
26 እኛ እናውቅ ዘንድ ይህን ከመጀመሪያው የተናገረ፣
‘እርሱ ትክክል ነው’ እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረ ማነው?
ማንም አልተናገረም፤
ቀደም ብሎ የተናገረ የለም፤
ቃላችሁንም የሰማ የለም።
27 በመጀመሪያ፣ ‘እነሆ፤ ተመልከቺአቸ’
ብዬ ለጽዮን የተናገርሁ እኔ ነበርሁ፤
ለኢየሩሳሌምም
የምሥራች ነጋሪን ሰጥቻለሁ።
28 ተመለከትሁ ማንም አልነበረም፤
ከመካከላቸው አማካሪ የለም፤
ስጠይቅም መልስ የሚሰጥ የለም።
29 እነሆ፤ ሁሉም ከንቱ ናቸው፤
ሥራቸውም መና ነው፤
ምስሎቻቸውም ባዶ ነፋስ ናቸው።