1 “ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣
ነገሥታትን ትጥቅ አስፈታ ዘንድ፣
ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣
ደጆች እንዳይዘጉ፣
በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣
ለቂሮስእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
2 ‘በፊትህ እሄዳለሁ፤
ተራሮችንእደለድላለሁ፤
የናስ በሮችን እሰብራለሁ፤
የብረት መወርወሪያዎችንም እቈርጣለሁ።
3 በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣
እኔእግዚአብሔርመሆኔን ታውቅ ዘንድ፣
በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣
በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
4 ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣
ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣
አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣
በስምህ ጠርቼሃለሁ፤
የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።
5 እኔእግዚአብሔርነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤
ከእኔ በቀር አምላክ የለም።
አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣
እኔ አበረታሃለሁ።
6 ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣
እስከ መጥለቂያው፣
ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤
እኔእግዚአብሔርነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም።
7 እኔ ብርሃንን ሠራሁ፤ ጨለማንም ፈጠርሁ፤
አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤
ይህን ሁሉ የማደርግ እኔእግዚአብሔርነኝ።’
8 “እናንት ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤
ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤
ምድር ትከፈት፤
ድነት ይብቀል፤
ጽድቅም አብሮት ይደግ፤
እኔእግዚአብሔርፈጥሬዋለሁ።
9 “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣
ከሠሪው ጋር ክርክር ለሚገጥም ወዮለት፤
ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣
‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን?
የምትሠራውስ ሥራ፣
‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?
10 አባቱን፣
‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣
እናቱንም፣
‘ምን ወለድሽ’? ለሚል ወዮለት።
11 “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነእግዚአብሔር፣
ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤
‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?
ስለ እጆቼስ ሥራ ታዙኛላችሁን?
12 ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤
ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤
እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤
የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።
13 ቂሮስንበጽድቅ አስነሥቻለሁ፤
መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤
ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤
ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣
ነጻ ያወጣል፤’
ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።”
14 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“የግብፅ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣
ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣
ወደ አንተ ይመጣሉ፤
የአንተ ይሆናሉ፤
ከኋላ ይከተሉሃል፤
በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣
በፊትህ እየሰገዱ፣
‘በእውነትእግዚአብሔርከአንተ ጋር ነው፤
ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”
15 አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤
አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።
16 ጣዖት ሠሪዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀላሉ፤
በአንድነት ይዋረዳሉ።
17 እስራኤል ግንበእግዚአብሔር፣
በዘላለም ድነት ይድናል፤
እናንተም ለዘላለም፣
አታፍሩም፤ አትዋረዱም።
18 ሰማያትን የፈጠረ፣
እርሱእግዚአብሔርነው፤
ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣
የመሠረታት፣
የሰው መኖሪያ እንጂ፣
ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣
እግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤
‘እኔእግዚአብሔርነኝ፤
ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
19 በጨለማ ምድር፣
በምስጢር አልተናገርሁም፤
ለያዕቆብም ዘር፣
“በከንቱ ፈልጉኝ” አላልሁም።
እኔእግዚአብሔርእውነትን እናገራለሁ፤
ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለው።’
20 “በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤
እናንት ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ።
የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣
ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።
21 ጒዳያችሁን ተናገሩ፤ አቅርቡ፤
ተሰብስበውም ይማከሩ።
ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ?
ከጥንትስ ማን ተናገረ?
እኔእግዚአብሔርአይደለሁምን?
ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣
ከእኔ በቀር ማንም የለም፤
ከእኔ ሌላአምላክየለም።
22 “እናንት የምድር ዳርቻ ሁሉ፣
እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤
ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።
23 ጒልበት ሁሉ በእኔ ፊት ይንበረከካል፤
አንደበትም ሁሉ በእኔ ይምላል፤
ብዬ በራሴ ምያለሁ፤
የማይታጠፍ ቃል፣
ከአፌ በጽድቅ ወጥቶአል።
24 ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣
በእግዚአብሔርብቻ ነው’ ይላሉ።”
በእርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣
ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ።
25 ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣
በእግዚአብሔርይጸድቃሉ፤
ሞገስንም ያገኛሉ።