ኢሳይያስ 5

ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ቅኔ

1 ስለ ወዳጄ፣

ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤

ወዳጄ በለምለም ኰረብታ ላይ

የወይን ቦታ ነበረው።

2 መሬቱን ቈፈረ፤ ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤

ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት።

በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤

የወይን መጭመቂያ ጒድጓድም አበጀ፤

ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ አሰበ፤

ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ።

3 “እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤

በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ።

4 ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን

ሊደረግለት ይገባ ነበር?

መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ

ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?

5 እንግዲህ በወይኔ ቦታ

ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤

ዐጥሩን እነቅላለሁ፤

ለጥፋት ይጋለጣል፤

ግንቡንም አፈርሳለሁ፣

መረጋገጫም ይሆናል።

6 የማይኰተኰትና የማይታረም

ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤

ኵርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤

ዝናብም እንዳይዘንብበት

ደመናዎችን አዝዛለሁ።”

7 የሰራዊት ጌታየእግዚአብሔር

የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤

የይሁዳ ሰዎችም

የደስታው አትክልት ናቸው።

ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤

ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።

ወዮታና ፍርድ

8 ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ፣

ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፣

መሬትን ከመሬት ጋር በማያያዝ፣

ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ

9 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤

“ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፣

የሚያማምሩም ቤቶች ኗሪ ያጣሉ።

10 ከሩብ ጋሻየወይን ቦታ አንድ የባዶስ መስፈሪያ ያህል የወይን ጭማቂ ብቻ ይገኛል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር ተዘርቶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ብቻ ይሰጣል።

11 የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ

ማልደው ለሚነሡ፣

እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት

ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸ

12 በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፣

ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤

ነገር ግንለእግዚአብሔርሥራ ቦታ አልሰጡም፤

ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም።

13 ስለዚህ ሕዝቤ

ዕውቀት በማጣቱ ይማረካል፤

መኳንንቱም በራብ ይሞታሉ፤

ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል።

14 ስለዚህ ሲኦልሆዷን አሰፋች፣

አፏንም ያለ ልክ ከፈተች፤

መኳንንቱና ሕዝቡ ከረብሸኞቻቸውና ከጨፋሪዎቻቸው ጋር

ወደዚያ ይወርዳሉ።

15 ሰው ይዋረዳል፤

የሰው ልጅም ዝቅ ዝቅ ይላል፤

የእብሪተኛውም ዐይን ይሰበራል።

16 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤

ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል።

17 በጎችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደሚሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤

የበግ ጠቦቶችም በባለጠጎች ፍርስራሽ ላይ ሣር ይበላሉ።

18 ኀጢአትን በማታለል ገመድ ለሚስቡ፣

በደልንም በሠረገላ ማሰሪያ ለሚጐትቱ ወዮላቸው!

19 በዐይናችን እንድናይ

እግዚአብሔርይቸኵል፤

ሥራውንም ያፋጥን፤

የእስራኤልን ቅዱስ፣ የእርሱን ዕቅድ

እንድናውቃት ትቅረብ፤

ትምጣም ለሚሉ ወዮላቸው!”

20 ክፉውን መልካም፣

መልካሙን ክፉ ለሚሉ

ብርሃኑን ጨለማ፣

ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፣

ጣፋጩን መራራ፣

መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!

21 ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፣

በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!

22 የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፣

የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው!

23 ጒቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፣

ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!

24 ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣

ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣

የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤

አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበናል፤

የሰራዊት ጌታየእግዚአብሔርንሕግ ንቀዋልና፤

የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃለዋል።

25 የእግዚአብሔርቍጣ በሕዝቡ ላይ ነዶአል፤

እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤

ተራሮች ራዱ፤

ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቍጣው ገና አልተመለሰም፤

እጁም እንደ ተነሣ ነው።

26 ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን

ምልክት ያቆማል፤

ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤

እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ።

27 በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤

የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤

የወገባቸው መቀነት አይላላም፤

የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም።

28 ፍላጻቸው የተሳለ፣

ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤

የሠረገሎቻቸውም መንኰራኵሮች እንደ

ዐውሎ ነፋስ ናቸው።

29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤

እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤

ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤

ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም።

30 በዚያን ቀን

እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤

ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፣

ጨለማንና መከራን ያያል፤

ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *