የዘላለም ድነት ለጽዮን
1 “እናንት ጽድቅን የምትከታተሉ፣
እግዚአብሔርንየምትፈልጉ ስሙኝ፤
ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣
ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጒድጓድ ተመልከቱ።
2 ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣
ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤
በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤
ባረክሁት፤ አበዛሁትም።
3 እግዚአብሔርጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤
ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤
ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣
በረሓዋንም እንደእግዚአብሔርተክል ቦታ ያደርጋል፤
ተድላና ደስታ፣
ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በእርሷ ይገኛሉ።
4 “ወገኔ ሆይ፤ አድምጠኝ፤
ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤
ሕግ ከእኔ ይወጣል፤
ፍርዴም ለሕዝቦች ብርሃን ይሆናል።
5 ጽድቄ በፍጥነት እየቀረበ፣
ማዳኔም እየደረሰ ነው፤
ክንዴም ለመንግሥታት ፍትሕን ያመጣል፤
ደሴቶች ወደ እኔ ይመለከታሉ፤
ክንዴንም በተስፋ ይጠብቃሉ።
6 ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፤
ወደ ታች ወደ ምድርም ተመልከቱ፤
ሰማያት እንደ ጢስ በነው ይጠፋሉ፤
ምድር እንደ ልብስ ታረጃለች፤
ነዋሪዎቿም እንደ አሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፤
ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤
ጽድቄም መጨረሻ የለውም።
7 “እናንት ጽድቅን የምታውቁ፣
ሕጌንም በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች ስሙኝ፤
ሰዎች ሲዘብቱባችሁ አትፍሩ፤
ሲሰድቧችሁ አትደንግጡ።
8 ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋል፤
ትል እንደ በግ ጠጒር ይውጣቸዋል፤
ጽድቄ ግን ለዘላለም፣
ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንታ ትኖራለች።”
9 የእግዚአብሔርክንድ ሆይ፤
ተነሥ፤ ተነሥ! ኀይልን ልበስ፤
እንዳለፉት ዘመናት፣
በጥንት ትውልዶችም እንደሆነው ሁሉ ተነሥ።
ረዓብን የቈራረጥህ፣
ታላቁን ዘንዶ የወጋህ አንተ አይደለህምን?
10 የዳኑት እንዲሻገሩ ባሕሩን፣
የታላቁን ጥልቅ ውሆች ያደረቅህ፣
በጥልቁም ውስጥ መንገድ ያበጀህ፣
አንተ አይደለህምን?
11 እግዚአብሔርየተቤዣቸው ይመለሳሉ፤
በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤
የዘላለማዊ ደስታን አክሊል ይቀዳጃሉ፤
ተድላና ደስታ ያገኛሉ፤
ሐዘንና ልቅሶም ከእነርሱ ይሸሻል።
12 “የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤
ሟች የሆኑትን ሰዎች፣
እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች
ለምን ትፈራለህ?
13 የፈጠረህን፣
ሰማያትን የዘረጋውን፣
ምድርን የመሠረተውንእግዚአብሔርንረስተሃል፤
ሊያጠፋህ ከተዘጋጀው፣
ከጨቋኙ ቊጣ የተነሣ፣
በየቀኑ በሽብር ትኖራለህ፤
ታዲያ የጨቋኙ ቊጣ የት አለ?
14 ዐንገታቸውን የደፉ እስረኞች በፍጥነት ነጻ ይወጣሉ፤
በታሰሩበትም ጒድጓድ ውስጥ አይሞቱም፤
እንጀራ አያጡም።
15 ሞገዱ እንዲተም ባሕሩን የማናውጥ፣
እኔእግዚአብሔርአምላክህ ነኝና፤
ስሙም የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርነው።
16 ቃሌን በአፍህ አኖርሁ፤
በእጄ ጥላ ጋረድሁህ፤
ሰማያትን በስፍራቸው ያስቀመጥሁ፣
ምድርን የመሠረትሁ፣
ጽዮንንም፣ ‘አንቺ ሕዝቤ ነሽ’ ያልሁ እኔ ነኝ።
የእግዚአብሔር የቊጣ ጽዋ
17 ከእግዚአብሔርእጅ፣
የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ፣
ዝቃጩ እንኳ ሳይቀር፣
ሰዎችን የሚያንገደግደውን ዋንጫ የጨለጥሽ፣
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤
ተነሺ፤ ተነሺ።
18 ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣
የመራት አንድም አልነበረም፤
ካሳደገቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ፣
እጇን ይዞ የወሰዳት ማንም አልነበረም።
19 እነሆ፤ በጥፋት ላይ ጥፋት መጥተውብሻል፤
ታዲያ ማን ያጽናናሻል?
እነርሱም መፈራረስና ጥፋት፣ ራብና ሰይፍናቸው፤
ታዲያ ማን ያስተዛዝንሽኀሀ
20 ወንዶች ልጆችሽ ዝለዋል፤
በወጥመድ እንደ ተያዘ ሚዳቋ፣
በየጐዳናው አደባባይ ላይ ተኝተዋል።
የእግዚአብሔርቊጣ፣
የአምላክሽም ተግሣጽ ሞልቶባቸዋል።
21 ስለዚህ አንቺ የተጐዳሽ፣
ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ ይህን ስሚ።
22 ሕዝቡን የሚታደግ አምላክሽ፣
ልዑልእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ ከእጅሽ፣
ያንገደገደሽን ጽዋ ወስጃለሁ፤
ያንን ጽዋ፣ የቊጣዬን ዋንጫ፣
ዳግም አትጠጪውም፤
23 ባስጨነቁሽ፣
‘በላይሽ ላይ እንድንሄድ ተነጠፊልን’
ባሉሽ እጅ ላይ አደርገዋለሁ፤
ጀርባሽን እንደ መሬት፣
እንደ መሸጋገሪያም መንገድ አደረግ ሽላቸው።”