1 ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤
ኀይልን ልበሺ፤
ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ!
የክብር ልብስሽን ልበሺ፤
ያልተገረዘ የረከሰም
ከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።
2 ትቢያሽን አራግፊ፤
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ በዙፋንሽ ላይ ተቀመጪ፤
ምርኮኛዪቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤
የዐንገትሽን የእስራት ሰንሰለት አውልቀሽ ጣዪ።
3 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ያለ ዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤
ያለ ገንዘብ ትቤዣላችሁ።”
4 ልዑልእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“በመጀመሪያ ሕዝቤ ይኖር ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፤
በኋላም አሦር ያለ ምክንያት አስጨንቆ ገዛው።
5 “አሁን እዚህ ምን አለኝ?” ይላልእግዚአብሔር፤
“ሕዝቤ ያለ ምክንያት ተወስዶአል፤
የገዟቸው ተሣልቀውባቸዋል”
ይላልእግዚአብሔር።
“ቀኑን ሙሉ፣
ስሜ ያለ ማቋረጥ ይሰደባል።
6 ስለዚህ ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤
በዚያ ቀንም፣
አስቀድሜ የተናገርሁ እኔ መሆኔን ይረዳል፤
እነሆ፤ እኔው ነኝ።”
7 በተራሮች ላይ የቆሙ፣
የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣
ሰላምን የሚናገሩ፣
መልካም ዜና የሚያበስሩ፣
ድነትን የሚያውጁ፣
ጽዮንንም፣
“አምላክሽ ነግሦአል” የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።
8 ስሚ፤ ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገዋል፤
በአንድነት በእልልታ ይዘምራሉ።
እግዚአብሔርወደ ጽዮን ሲመለስ፣
በዐይኖቻቸው ያያሉ።
9 እናንት የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣
በአንድነት በእልልታ ዘምሩ፤
እግዚአብሔርሕዝቡን አጽናንቶአል፤
ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቶአልና።
10 እግዚአብሔርበመንግሥታት ሁሉ ፊት፣
የተቀደሰ ክንዱን ይገልጣል፤
በምድር ዳርቻዎች ያሉ ሁሉ፣
የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።
11 እናንትየእግዚአብሔርንዕቃ የምትሸከሙ፣
ተለዩ፤ ተለዩ፤ ከዚያ ውጡ፤
ርኵስ ነገር አትንኩ፤
ከዚያ ውጡ ንጹሓንም ሁኑ።
12 ሆኖም በችኰላ አትወጡም፤
ሸሽታችሁም አትሄዱም፤
እግዚአብሔርፊት ፊታችሁ ይሄዳል፤
የእስራኤልአምላክደጀን ይሆናችኋል።
የባሪያው ሥቃይና ክብር
13 እነሆ፤ ባሪያዬ የሚያከናውነው በማስተዋል ነው፤
ገናና ይሆናል፤ ከፍ ከፍ ይላል፤ እጅግ ይከብራልም።
14 ብዙዎች በእርሱእስኪደነግጡ ድረስ፣
መልኩ ከማንም ከሰው የተለየ፤
ከሰው ልጆችም ሁሉ ይልቅ ተጐሳቈለ።
15 ስለዚህ ብዙ መንግሥታትን ያስደንቃል፤
በእርሱ ምክንያት ነገሥታት አፋቸውን ይይዛሉ፤
ያልተነገራቸውን ያያሉ፤
ያልሰሙትን ያስተውላሉ።