ኢሳይያስ 53

1 የሰማነውን ነገር ማን አመነ?

የእግዚአብሔርስክንድ ለማን ተገለጠ?

2 በፊቱ እንደ ቡቃያ፣

ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤

የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤

እንድንወደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም።

3 በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣

የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር።

ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣

የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም።

4 በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤

ሕመማችንንም ተሸከመ፤

እኛ ግንበእግዚአብሔርእንደ ተመታ፣

እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው።

5 ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤

ስለ በደላችንም ደቀቀ፤

በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤

በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።

6 እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤

እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጐድን፤

እግዚአብሔርም፣ የሁላችንን በደል

በእርሱ ላይ ጫነው።

7 ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤

ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤

እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤

በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣

አፉን አልከፈተም።

8 በማስጨነቅናበፍርድ ተወሰደ፤

ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመቶ፣

ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ፣

ከትውልዱ ማን አስተዋለ?

9 በአፉ ተንኰል ሳይገኝበት፣

ምንም ወንጀል ሳይሠራ፣

አሟሟቱ ከክፉዎች፣

መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ሆነ።

10 መድቀቁና መሠቃየቱ ግንየእግዚአብሔርፈቃድ ነበር፤

እግዚአብሔርነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣

ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤

የእግዚአብሔርምፈቃድ በእጁ ይከናወናል።

11 ከነፍሱ ሥቃይ በኋላ፣

የሕይወት ብርሃንያያል፤ ደስም ይለዋል፤

ጻድቅ ባሪያዬ በዕውቀቱ ብዙዎቹን ያጸድቃል፤

መተላለፋቸውንም ይሸከማል።

12 ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆችጋር እሰጠዋለሁ፤

ምርኮውን ከኀያላንጋር ይካፈላል፤

እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣

ከክፉ አድራጊዎችም ጋር በመቈጠሩ፣

የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤

ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *