የወደፊቱ የጽዮን ክብር
1 “አንቺ መካን ሴት፤
አንቺ ልጅ ወልደሽ የማታውቂ፤
ዘምሪ፤ እልል በዪ፤ በደስታ ጩኺ፤
አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣
ባል ካላት ሴት ይልቅ፣
የፈቷ ልጆች ይበዛሉና”
ይላልእግዚአብሔር።
2 “የድንኳንሽን ቦታ አስፊ፤
የድንኳንሽን መጋረጃዎች በትልቁ ዘርጊ፤
ፈጽሞ አትቈጥቢ፤
ገመዶችሽን አርዝሚአቸው፤
ካስማዎችሽንም ቀብቅቢ።
3 ወደ ቀኝም ወደ ግራም ትስፋፊያለሽ፤
ዘሮችሽ መንግሥታትን ይወርሳሉ፤
በባድማ ከተሞቻቸውም ይኖራሉና።
4 “አይዞሽ አትፍሪ፤ ኀፍረት አይገጥምሽም፤
ውርደት ስለማይደርስብሽ አትሸማቀቂ፤
የወጣትነት ኀፍረትሽን ትረሺዋለሽ፤
የመበለትነት ስድብሽንም ከእንግዲህ አታስታውሺውም።
5 ባልሽ ፈጣሪሽ ነውና፤
ስሙም የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርነው፤
ታዳጊሽ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤
እርሱም የምድር ሁሉአምላክይባላል።
6 እንደ ተናቀች የልጅነት ሚስት፣
ከልብ እንዳዘነችና እንደ ተጠላች ሚስት፣
እግዚአብሔርእንደ ገና ይጠራሻል”
ይላልአምላክሽ።
7 “ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤
ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።
8 ለጥቂት ጊዜ እጅግ ስለ ተቈጣሁ፣
ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፤
ነገር ግን በዘላለማዊ ቸርነቴ፣
እራራልሻለሁ”
ይላል ታዳጊሽእግዚአብሔር።
9 “ይህ ለእኔ የኖኅ ውሃ ምድርን ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቃት እንደማልሁበት፣
እንደ ኖኅ ዘመን ነው፤
አሁንም አንቺን ዳግም እንዳልቈጣ፣
እንዳልገሥጽሽም ምያለሁ።
10 ተራሮች ቢናወጡ፣
ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣
ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤
የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም”
ይላል መሓሪሽእግዚአብሔር።
11 “አንቺ የተጨነቅሽ ከተማ ሆይ፤ በዐውሎ ነፋስ የተናወጥሽ፣ ያልተጽናናሽም፤
እነሆ፤ በከበሩ ድንጋዮችአስጊጬ እገነባሻለሁ፤
በሰንፔር ድንጋይም እመሠርትሻለሁ።
12 ጒልላትሽን በቀይ ዕንቊ፣
በሮችሽን በሚያብረቀርቁ ዕንቊዎች፣
ቅጥሮችሽንም በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።
13 ወንዶች ልጆችሽ ሁሉከእግዚአብሔርየተማሩ ይሆናሉ፤
የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።
14 በጽድቅ ትመሠረቻለሽ፤
የግፍ አገዛዝ ከአንቺ ይርቃል፤
የሚያስፈራሽ አይኖርም፤
ሽብር ከአንቺ ይርቃል፤
አጠገብሽም አይደርስም።
15 ማንም ጒዳት ቢያደርስብሽ፣ ከእኔ አይደለም፤
ጒዳት ያደረሰብሽ ሁሉ ለአንቺ እጁን ይሰጣል።
16 “እነሆ የከሰሉ ፍም እንዲቀጣጠል የሚያራግበውን፣
የጦር መሣሪያ የሚያበጀውን፣ አንጥረኛውን የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤
ጥፋት እንዲያደርስም የፈጠርሁ እኔ ነኝ
አጥፊውንም የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤
17 በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤
የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤
እንግዲህየእግዚአብሔርባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤
ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤”
ይላልእግዚአብሔር።