ለሌሎች የተሰጠ ድነት
1 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ፍትሕን ጠብቁ፤
መልካሙን አድርጉ፤
ማዳኔ በቅርብ ነው፤
ጽድቄም ፈጥኖ ይገለጣልና።
2 ሰንበትን ሳያረክስ የሚያከብር፣
ክፉን ከማድረግ እጁን የሚሰበስብ፣ የሚገታ፣
እነዚህን የሚፈጽም ሰው የተባረከ ነው።”
3 ወደእግዚአብሔርየተጠጋ መጻተኛ፣
“እግዚአብሔር በርግጥ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤
ጃንደረባም፣
“እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል።
4 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ሰንበቶቼን ለሚያከብሩ ጃንደረቦች፣
ደስ የሚያሰኘኝን ለሚመርጡ፣
ቃል ኪዳኔን፣ ለሚጠብቁ
5 በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣
ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣
መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤
ለዘላለም፣
የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።
6 እርሱን ለማገልገል፣
ራሳቸውንከእግዚአብሔርጋር ያቈራኙ መጻተኞች፣
የእግዚአብሔርንስም በመውደድ፣
እርሱንም በማምለክ፣
ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣
ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣
7 ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤
በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።
የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣
በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤
ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ
የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”
8 የተበተኑትን እስራኤል የሚሰበስብ፣
ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ከተሰበሰቡት በተጨማሪ፣
ሌሎችን እንደ ገና እሰበስባለሁ።”
በክፉዎች ላይ የእግዚአብሔር ወቀሳ
9 እናንት የምድር አራዊት ሁሉ ኑ፤
እናንት የዱር አራዊት ሁሉ ኑና በጥርሳቸሁ ቦጫጭቁ።
10 የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤
ዕውቀት የላቸውም፤
ሁሉም ድምፅ የለሽ ውሾች ናቸው፤
መጮኽ አይችሉም፤
ተጋድመው ያልማሉ፤
እንቅልፋሞች ናቸው።
11 እጅግ ሲበዛ ሆዳም ውሾች ናቸው፤
ጠገብሁን አያውቁም፤
የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤
ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ሄዱ፤
እያንዳንዳቸውም የግል ጥቅማቸውን ፈለጉ።
12 እርስ በርሳቸውም፣ “ኑና የወይን ጠጅ እንገባበዝ፤
እስክንሰክር እንጠጣ፤
ነገም ያው እንደ ዛሬ፣
ምናልባትም የተሻለ ቀን ይሆንልናል” ይባባላሉ።