የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት
1 የጌታየእግዚአብሔርመንፈስ በእኔ ላይ ነው፤
ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣
እግዚአብሔርቀብቶኛል።
ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣
ለምርኮኞች ነጻነትን፣
ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅልኮኛል፤
2 የተወደደውንየእግዚአብሔርንዓመት፣
የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣
የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤
3 በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣
በዐመድ ፈንታ፣
የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣
በልቅሶ ፈንታ፣
የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስላቸው፣
በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣
የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤
እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣
እግዚአብሔርየተከላቸው፣
የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
4 የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤
በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤
ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትን
ፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።
5 መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤
ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል።
6 እናንተምየእግዚአብሔርካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤
የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤
የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤
በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።
7 ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣
ዕጥፍ ይቀበላሉ፤
በውርደታቸው ፈንታ፣
በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤
የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤
ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
8 “እኔእግዚአብሔርፍትሕን ስለምወድ፣
ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤
በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤
ከእነርሱም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
9 ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣
ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤
የሚያዩአቸውም ሁሉ፣
እግዚአብሔርየባረካቸው ሕዝብ እንደሆኑ ያውቃሉ።
10 በእግዚአብሔርእጅግ ደስ ይለኛል፤
ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤
ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣
ሙሽራዪቱም በዕንቆቿ እንደምታጌጥ፣
የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤
የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
11 ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣
የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣
ጌታእግዚአብሔርምበመንግሥታት ሁሉ ፊት፣
ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።