ኢሳይያስ 7

የአማኑኤል ምልክትነት

1 የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም።

2 ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ።

3 እግዚአብሔርምኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብአካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤

4 እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጒማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር።

5 ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤

6 “ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።”

7 ልዑልእግዚአብሔርግን እንዲህ ይላል፦

“ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤

ከቶም አይደረግም፤

8 የሶርያ ራስ ደማስቆ፣

የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤

በሥልሳ አምስት ዓመት ውስጥ፣

የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ

መሆኑም ይቀራል።

9 የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣

የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው።

እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣

ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ”

10 እንደ ገናምእግዚአብሔርአካዝን እንዲህ አለው፤

11 “ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህከእግዚአብሔርከአምላክህ ለምን።”

12 አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣እግዚአብሔርንምአልፈታተንም” አለ።

13 ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን?

14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤልብላ ትጠራዋለች።

15 ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል።

16 ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል።

17 ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮእግዚአብሔርከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።”

18 በዚያን ቀንእግዚአብሔርራቅ ካሉት ከግብፅ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል።

19 እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጒድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ።

20 በዚያን ቀን፣ እግዚአብሔር ከወንዝማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጒራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል።

21 በዚያን ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል።

22 ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ።

23 በዚያን ቀን ሺህ ሰቅልብር የሚያወጣ አንድ ሺህ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል።

24 ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤

25 ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *