አሦር የእግዚአብሔር መሣሪያ
1 እግዚአብሔርምእንዲህ አለኝ፤ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ፣ ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’ብለህ በተለመደው በሰው ፊደል ጻፍበት።
2 እኔም፣ ካህኑን ኡሪያንንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ታማኝ ምስክሮቼ እንዲሆኑ እጠራቸዋለሁ።”
3 እኔም ወደ ነቢዪቱ ሄድሁ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች።እግዚአብሔርም፣እንዲህ አለኝ፤ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው።
4 ሕፃኑም፣ ‘አባባ’ ወይም ‘እማማ’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት፣ የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳል።”
5 እግዚአብሔርምእንደ ገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤
6 “ይህ ሕዝብ በጸጥታ የሚፈሰውን
የሰሊሆምን ውሆች ትቶ፣
በረአሶንና
በሮሜልዩ ልጅ ተደስቶአልና።
7 ስለዚህ ጌታ ታላቁንና ብርቱውን
የጐርፍ ውሃ፣
የአሦርን ንጉሥ ከነግርማ ሞገሱ ሁሉ ያመጣባቸዋል።
ውሃውም ከቦዩ ዐልፎ ተርፎ
በወንዙ ዳር ያለውን ምድር ሁሉ ያጥለቀልቃል፤
8 እየጠራረገ ወደ ይሁዳ ይወርዳል፤
እያጥለቀለቀ ያልፋል፤
እስከ ዐንገትም ይደርሳል፤
አማኑኤልሆይ፤
የተዘረጉ ክንፎቹ ምድርህን ከዳር እስከ
ዳር ይሸፍናሉ።”
9 እናንተ አሕዛብ፣ ፎክሩ፤
ግን ደንግጡ።
በሩቅ አገር ያላችሁ አድምጡ፤
ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤
ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤
10 ተመካከሩ፤ ግን አይሳካም፤
ዕቅድ አውጡ፤ ሆኖም አይጸናም፤
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።
እግዚአብሔርን ፍሩ
11 እግዚአብሔርብርቱ እጁን በላዬ አድርጎ የእነዚህን ሰዎች መንገድ እንዳልከተል አስጠነቀቀኝ፤ እንዲህም አለኝ፤
12 “እነዚህ ሰዎች፣ ‘አድማ’ ብለው የሚጠሩትን፣
ማንኛውንም ነገር፣ ‘አድማ’ አትበሉ፤
እነርሱ የሚፈሩትን አትፍሩ፤
አትሸበሩለትም።
13 ልትቀድሱ የሚገባው የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርንብቻ ነው፤
ልትፈሩት የሚገባው እርሱን ነው፤
ልትንቀጠቀጡለት የሚገባውም እርሱ ነው።
14 እርሱም መቅደስ ይሆናል፤
ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግን
የሚያደናቅፍ ድንጋይ
የሚያሰናክልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤
ለኢየሩሳሌም ሕዝብም
ወጥመድና አሽክላ ይሆናል።
15 ከእነርሱ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤
ይወድቃሉ፤ ይሰበራሉ፤
ወጥመድ ይገባሉ፤ ይያዛሉም።”
16 ምስክርነቱን አሽገው፤
ሕጉንም በደቀ መዛሙርቴ መካከል አትመው።
17 ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሸሸገውን
እግዚአብሔርንእጠብቃለሁ፤
እርሱንም ተስፋ አደርጋለሁ።
18 እነሆ፤ እኔናእግዚአብሔርየሰጠኝ ልጆች በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሰራዊት ጌታከእግዚአብሔርለእስራኤል ምልክትና ድንቅ ነን።
19 ሰዎች፣ “የሚያነበንቡትንና የሚያሾካ ሹኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?
20 ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም።
21 ተጨንቀውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ክፉኛ ሲራቡም ይቈጣሉ፤ ወደ ላይ እየተመለከቱ ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይራገማሉ።
22 ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ የሚያዩትም ጭንቀት፣ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።