ኤርምያስ 12

የኤርምያስ ማጒረምረም

1 እግዚአብሔርሆይ፤ ጒዳዬን በፊትህ ሳቀርብ፣

አንተ ጻድቅ መሆንህን እያወቅሁ ነው።

የክፉዎች መንገድ ለምን ይሰምራል?

የከዳተኞችስ ኑሮ ለምን ይሳካል?

2 አንተ ተክለሃቸዋል፤ ሥርም ሰደዋል፤

አድገዋል፤ ፍሬም አፍርተዋል።

ሁል ጊዜ አንተ በአፋቸው ላይ አለህ፤

ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ።

3 ነገር ግንእግዚአብሔርሆይ፤ አንተ እኔን ታውቀኛለህ፤ ታየኛለህ፤

ስለ አንተም ያለኝን ሐሳብ ትመረምራለህ።

እንደሚታረዱ በጎች ንዳቸው፤

ለዕርድም ቀን ለይተህ አቈያቸው፤

4 ምድሪቱ በዝናብ እጦት የምትጐዳው፣

የሜዳውም ሣር ሁሉ በድርቅ የሚመታው እስከ መቼ ነው?

ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣

እንስሳትና አዕዋፍ ጠፍተዋል፤

ደግሞም ሕዝቡ፣

“በእኛ ላይ የሚሆነውን አያይም” ብለዋል።

የእግዚአብሔር ምላሽ

5 “ከእግረኞች ጋር ሮጠህ፣

እነርሱ ካደከሙህ፣

ከፈረሰኞች ጋር እንዴት ልትወዳደር ትችላለህ?

በሰላም አገር ከተሰናከልህ፣

በዮርዳኖስ ደን ውስጥ እንዴት ልትሆን ነው?

6 ወንድሞችህና የገዛ ቤተ ሰብህ፣

እነርሱ እንኳ አሢረውብሃል፣

በአንተም ላይ ይጮኻሉ፤

በመልካም ቢናገሩህም እንኳ

አትመናቸው።

7 “ቤቴን እተዋለሁ፤

ርስቴን እጥላለሁ፤

የምወዳትን እርሷን፣

አሳልፌ በጠላቶቿ እጅ እሰጣታለሁ።

8 ርስቴ፣ በዱር እንዳለ አንበሳ

ተነሥታብኛለች

በእኔም ላይ ጮኻብኛለች፤

ስለዚህ ጠላኋት።

9 ርስቴ ሌሎች አሞሮች፣

ሊበሏት እንደ ከበቧት፣

እንደ ዝንጒርጒር አሞራ አልሆነችምን?

ሂዱ፤ የዱር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፤

እንዲቀራመቷትም አምጧቸው።

10 ብዙ እረኞች የወይን ቦታዬን ያጠፋሉ፤

ይዞታዬንም ይረግጣሉ፤

ደስ የምሰኝበትንም ማሳ፣

ጭር ያለ በረሓ ያደርጉታል።

11 በፊቴ ባድማ፣

ደረቅና ወና ይሆናል፤

መላዪቱም ምድር ጠፍ ትሆናለች፤

ስለ እርሷ የሚገደው የለምና።

12 በምድረ በዳ ባሉት ወና ኰረብቶች ላይ፣

አጥፊዎች ይሰማራሉ፤

የእግዚአብሔርሰይፍ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ፣

አንዳች ሳያስቀር ይበላል፤

የሚተርፍም የለም።

13 ስንዴን ይዘራሉ፤ እሾኽን ያጭዳሉ፤

ይደክማሉ፤ የሚያገኙት ግን የለም፤

ከእግዚአብሔርምጽኑ ቍጣ የተነሣ፣

በመኸራችሁ ውጤት ታፍራላችሁ።”

14 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ለሕዝቤ ለእስራኤል የሰጠሁትን ርስት የሚይዙትን ክፉ ጎረቤቶቼን ሁሉ፣ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅላለሁ፤

15 ከነቀልኋቸው በኋላ ግን መልሼ እምራቸዋለሁ፤ እያንዳንዳቸውንም ወደ ገዛ አገራቸውና ወደ ገዛ ርስታቸው መልሼ አመጣቸዋለሁ፤

16 የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩና ሕዝቤን በበኣል እንዲምል እንዳስ ተማሩት ሁሉ፣ ‘ሕያውእግዚአብሔርን’ ብለው በስሜ ቢምሉ፣ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ፤

17 የማይሰማኝን ሕዝብ ግን ፈጽሜ እነቅለዋለሁ፤ አጠፋዋለሁም” ይላልእግዚአብሔር።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *