ኤርምያስና ጳስኮር
1 በእግዚአብሔርቤተ መቅደስ ውስጥ አለቃ የነበረው፣ የኢሜር ልጅ ካህኑ ጳስኮር እነዚህን ነገሮች ኤርምያስ እንደ ተነበየ በሰማ ጊዜ፣
2 ነቢዩ ኤርምያስን መታው፣በእግዚአብሔርምቤተ መቅደስ በላይኛው የብንያም በር በእግር ግንድ ጠረቀው።
3 በማግስቱም ጳስኮር ኤርምያስን ከተጠረቀበት ግንድ አወጣው፤ ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔርከእንግዲህ ማጎርሚሳቢብብሎ ይጠራሃል እንጂ ጳስኮር አይልህም፤
4 እግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤ ‘አንተንና ባልንጀሮችህን ሁሉ ለሽብር እዳርጋለሁ፤ የገዛ ዐይንህ እያየ በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። ይሁዳን ሁሉ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል፤ በሰይፍም ይገድላቸዋል።
5 የዚህችን ከተማ ሀብት ሁሉ፣ ጥሪቷን፣ የይሁዳን ነገሥታት ውድ ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ።
6 ጳስኮር ሆይ፤ አንተና በቤትህ የሚኖሩት ሁሉ ወደ ባቢሎን ትጋዛላችሁ። አንተና በሐሰት ትንቢት የተነበይህላቸው ባልንጆሮችህ በዚያ ትሞታላችሁ፤ በዚያም ትቀበራላችሁ።’ ”
የኤርምያስ ማጒረምረም
7 እግዚአብሔርሆይ፤ አታለልኸኝ፤እኔም ተታለልሁ፤
አንተ ከእኔ እጅግ በረታህ፤ አሸነፍህም፤
ቀኑን ሙሉ ማላገጫ ሆንሁ፤
ሁሉም ተዘባበቱብኝ።
8 በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤
“ሁከትና ጥፋት!” ብዬ ዐውጃለሁ፤
ስለዚህየእግዚአብሔርቃል፣
ቀኑን ሙሉ ስድብና ነቀፋ አስከተለብኝ።
9 ነገር ግን፣ “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም፤
በስሙም አልናገርም” ብል፣
ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣
በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤
ዐፍኜ መያዝ አቃተኝ፤
ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም።
10 “በየቦታው ሽብር አለ፤
አውግዙት፤ እናውግዘው፤”
ብለው ብዙ ሲያንሾካሽኩ ሰማሁ፤
መውደቄን በመጠባበቅ፣
ባልንጀሮቼ የነበሩ ሁሉ፣
“ይታለል ይሆናል፣
ከዚያም እናሸንፈዋለን፤
እንበቀለዋለንም” ይላሉ።
11 ነገር ግንእግዚአብሔርእንደ ኀያል ተዋጊ ከእኔ ጋር ነው፤
ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ እንጂ አያሸንፉም፤
ክፉኛ ይዋረዳሉ እንጂ አይሳካላቸውም፤
ውርደታቸውም ከቶ አይረሳም።
12 ጻድቁን የምትፈትን ልብንና አእምሮን የምትመረምር፣
የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርሆይ፤
ጒዳዬን ለአንተ አሳልፌ ሰጥቻለሁና
ስትበቀላቸው ለማየት አብቃኝ።
13 ለእግዚአብሔርዘምሩ፤
ለእግዚአብሔርምስጋናን አቅርቡ፤
የችግረኛውን ነፍስ፣
ከክፉዎች እጅ ታድጎአልና።
14 የተወለድሁባት ዕለት የተረገመች ትሁን፤
እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን አትባረክ።
15 “ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል” ብሎ፣
ለአባቴ የምሥራች የነገረ፣
ደስ ያሰኘውም ሰው የተረገመ ይሁን።
16 ያ ሰውእግዚአብሔርሳይራራ፣
እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፤
በማለዳ ዋይታን፣
በቀትርም የጦርነትን ውካታ ይስማ፤
17 እናቴ መቃብር ትሆነኝ ዘንድ፣
ማሕፀንም ሰፊ የዘላለም ማደሪያዬ እንዲሆን፣
ከማሕፀንም ሳልወጣ አልገደለኝምና።
18 ችግርና ሐዘንን ለማየት፣
ዘመኔንም በውርደት ለመፈጸም፣
ለምን ከማሕፀን ወጣሁ?