በክፉዎች ነገሥታት ላይ የተሰጠ ፍርድ
1 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውረድ፤ ይህንም መልእክት በዚያ እንዲህ ብለህ ተናገር፤
2 ‘በዳዊት ዙፋን የተቀመጥህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተና መኳንንትህ፣ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፣የእግዚአብሔርንቃል ስሙ።
3 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
4 እነዚህን ትእዛዛት በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም።
5 ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤ ይላልእግዚአብሔር።’ ”
6 ስለዚህእግዚአብሔርስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤
“አንተ ለእኔ እንደ ገለዓድ፣
እንደ ሊባኖስ ተራራ ጫፍ ውብ ብትሆንም፣
በርግጥ እንደ ምድረ በዳ፣
ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።
7 በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሚይዙትን፣
አጥፊዎችን በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ።
ምርጥ የዝግባ ዛፎችን ይቈርጣሉ፤
ወደ እሳትም ይጥሏቸዋል።
8 “ከተለያየ አገር የመጡ ሕዝቦች በዚህች ከተማ በኩል ሲያልፉ፣ ‘እግዚአብሔርበዚህች ታላቅ ከተማ ላይ ለምን እንዲህ አደረገ?’ እያሉ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፤
9 ከዚያም፣ ‘የአምላካቸውንየእግዚአብሔርንኪዳን ትተው ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው’ ይላሉ።”
10 ከእንግዲህ ስለማይመለስ፣
የተወለደባትንም ምድር ዳግመኛ ስለማያይ፣
ለተማረከው ንጉሥ አምርራችሁ አልቅሱ እንጂ፣
ቀድሞ ለሞተው አታልቅሱ፤ አትዘኑም።
11 በአባቱ ምትክ በይሁዳ ላይ ስለ ነገሠው፣ ከዚህ ስፍራ በምርኮ ስለ ተወሰደው፣ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎእግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤ “ከእንግዲህ አይመለስም፤
12 ተማርኮ በሄደበት አገር ይሞታል እንጂ ይህቺን ምድር ዳግመኛ አያይም።”
13 “ቤተ መንግሥቱን በግፍ ለሚሠራ፣
ሰገነቱንም ፍትሕ በማዛባት ለሚገነባ፣
ወገኑን በነጻ ለሚያሠራ፣
የድካሙንም ዋጋ ለማይከፍለው፣
14 ‘ባለ ትልልቅ ሰገነት፣
ሰፊ ቤተ መንግሥት ለራሴ እሠራለሁ’ ለሚል ወዮለት!
ሰፋፊ መስኮቶችን ያበጅለታል፤
በዝግባ እንጨት ያስጌጠዋል፤
ቀይ ቀለምም ይቀባዋል።
15 “በዝግባ ዕንጨት ብዛት፣
የነገሥህ ይመስልሃልን?
አባትህስ ፍትሕንና ጽድቅን በማድረጉ፣
የሚበላውና የሚጠጣው ጐድሎት ነበርን?
እነሆ፣ ሁሉም መልካም ሆነለት።
16 የድኾችንና የችግረኞችን ፍትሕ አላጓደለም፤
ስለዚህም ሁሉ መልካም ሆነለት።
እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን?”
ይላልእግዚአብሔር።
17 “የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣
አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣
የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣
ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።
18 ስለዚህእግዚአብሔርስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፤
“ ‘ዋይ ወንድሜ! ዋይ፣ እኅቴን!’
ብለው አያለቅሱለትም።
‘ዋይ፣ ጌታዬን! ዋይ፣ ለግርማዊነቱ!’
ብለውም አያለቅሱለትም።
19 አህያ እንደሚቀበር ይቀበራል፤
ከኢየሩሳሌም በሮች ውጪ፤
ተጐትቶ ይጣላል።
20 “ሊባኖስ ላይ ወጥተሽ ጩኺ፤
ድምፅሽን በባሳን አሰሚ፤
በዓባሪም ሆነሽ ጩኺ፤
ወዳጆችሽ ሁሉ ወድመዋልና።
21 ተመችቶሽ በነበረ ጊዜ አስጠነቀቅሁሽ፤
አንቺ ግን፣ ‘አልሰማም’ አልሽ፤
ከትንሽነትሽ ጀምሮ መንገድሽ ይኸው ነበር፤
ቃሌንም አልሰማሽም።
22 እረኞችሽ ሁሉ በነፋስ ይወሰዳሉ፤
ወዳጆችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤
ከክፋትሽም ሁሉ የተነሣ፣
ታፍሪያለሽ፤ ትዋረጂያለሽም።
23 አንቺ፣ ‘በሊባኖስ’ውስጥ የምትኖሪ፣
መኖሪያሽን በዝግባ ዛፍ የሠራሽ ሆይ፤
ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣
መከራ በላይሽ ሲመጣ ጩኸትሽ እንዴት ይሆን!
24 “በሕያውነቴ እምላለሁ”፤ ይላልእግዚአብሔር“የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያንየቀኝ እጄ የቀለበት ማኅተም ብትሆን እንኳ ኖሮ፣ አውልቄ እጥልሃለሁ፤
25 ሕይወትህን ለሚሿት፣ ለምትፈራቸው ለባቢሎናውያንናለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጥሃለሁ።
26 አንተንና የወለደችህን እናትህን ወዳልተወለዳችሁበት ወደ ሌላ አገር ወርውሬ እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ትሞታላችሁ።
27 ልትመለሱባት ወደ ምትናፍቋት ምድር ከቶ አትመለሱም።”
28 ይህ ኢኮንያን የተባለ ሰው፣ የተናቀና የተሰበረ ገምቦ፣
ማንም የማይፈልገው ዕቃ ነውን?
እርሱና ልጆቹ ለምን ወደ ውጪ ተጣሉ?
ወደማያውቁትስ ምድር ለምን ተወረወሩ?
29 ምድር ሆይ፤ አንቺ ምድር፣ አንቺ ምድር፤
የእግዚአብሔርንቃል ስሚ!
30 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“አንድ እንኳ የረባ ዘር የማይወጣለት፣
አንድ እንኳ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጥ፣
ወይም በይሁዳ የሚገዛ የማይኖረው ነውና፤
በሕይወት ዘመኑ የማይከናወንለት፣
መካን ሰው ብላችሁ መዝግቡት።”