ኤርምያስ 27

የይሁዳ በናቡከደነፆር ሥር መውደቅ

1 በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህየእግዚአብሔርቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2 እግዚአብሔርምእንዲህ አለኝ፤ “የዕንጨት ቀንበር ሠርተህ በጠፍር ማነቆ አያይዘውና በዐንገትህ አስገባው፤

3 ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት ሰዎች በኩል ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ ለአሞን፣ ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት መልእክት ላክ።

4 ለጌቶቻቸውም እንዲያሳውቁ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ለጌቶቻችሁ ይህን ንገሯቸው፤

5 በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ ለምወደውም እሰጣለሁ።

6 አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ።

7 የእርሱ አገር በተራው ለሌሎች እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ለእርሱ፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት እርሱን ይገዙታል።

8 “ ‘ “ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር የማይገዛ፣ ዐንገቱንም ከቀንበሩ በታች ዝቅ የማያደርግ ማንኛውንም ሕዝብ ወይም መንግሥት በእጁ እስከማጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፣ በመቅሠፍትም እቀጣዋለሁ፤ ይላልእግዚአብሔር፤

9 ስለዚህ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤

10 ከምድራችሁ እንድትፈናቀሉ፣ እኔም እንዳሳድዳችሁና እንዳጠፋችሁ የሐሰት ትንቢት ይነግሯችኋልና።

11 ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዐንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሕዝብ በገዛ ምድሩ እንዲቀርና እያረሰም በዚያ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ይላልእግዚአብሔር።” ’ ”

12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም ይህንኑ መልእክት እንዲህ ብዬ ነገርሁት፤ “አንገታችሁን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዝቅ አድርጉ፤ እርሱንና ሕዝቡን አገልግሉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።

13 አንተና ሕዝብህ፣እግዚአብሔርለባቢሎን ንጉሥ አልገዛም ያለውን ሕዝብ ባስጠነቀቀበት በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ለምን ታልቃላችሁ?

14 ሐሰተኛ ትንቢት ስለሚነግሯችሁ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሙ፤

15 ‘እኔ አልላክኋቸውም’ ይላልእግዚአብሔር‘የሐሰት ትንቢት በስሜ ይናገራሉ፤ ስለዚህ እናንተንና ትንቢት የሚናገሩላችሁን ነቢያት አሳድዳለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።’ ”

16 እኔም ለካህናቱና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልሁ፤ “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔርቤት ዕቃ ከባቢሎን ቶሎ ይመለሳል’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሟቸው፤ የሚነግሯችሁ የሐሰት ትንቢት ነውና።

17 ስለዚህ እነርሱን መስማትትታችሁ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ባለመታዘዛችሁስ ይህቺ ከተማ ለምን ትፈራርስ?

18 እውነተኞች ነቢያት ከሆኑና በእርግጥየእግዚአብሔርቃል ካላቸው፣በእግዚአብሔርቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይወሰዱ ወደ ሰራዊት ጌታ ወደእግዚአብሔርእስቲ ይማልዱ!

19 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርበዚህች ከተማ ስለ ቀሩት፦ ዐምዶች፣ ከናስ ስለ ተሠራው ትልቁ ገንዳ፣ ስለ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችና ስለ ሌሎቹም ዕቃዎች እንዲህ ይላልና፤

20 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ መኳንንት ጋር ማርኮ ወደ ባቢሎን በወሰደ ጊዜ እነዚህ በከተማዪቱ የቀሩ ዕቃዎች ስለሆኑ፣

21 በእግዚአብሔርቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች፣ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

22 ‘ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቀመጣሉ’ ይላልእግዚአብሔር፤ ‘በዚያ ጊዜም እመልሳቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *