1 “በዚያ ዘመን” ይላልእግዚአብሔር፤ “ለእስራኤል ነገድ ሁሉ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”
2 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ፣
በምድረ በዳ ሞገስን ያገኛል፤
እኔም ለእስራኤል ዕረፍት ለመስጠት እመጣለሁ።”
3 እግዚአብሔርከሩቅተገለጠልን፤ እንዲህም አለን፤
“በዘላለማዊ ፍቅር ወድጄሻለሁ፤
ስለዚህም በርኅራኄ ሳብሁሽ።
4 የእስራኤል ድንግል ሆይ፤ እንደ ገና አንጽሻለሁ፤
አንቺም ትታነጪያለሽ፤
ከበሮችሽንም እንደ ገና አንሥተሽ፣
ከሚፈነጥዙት ጋር ትፈነድቂያለሽ።
5 እንደ ገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ፣
ወይን ትተክያለሽ፤
አትክልተኞች ይተክሏቸዋል፤
በፍሬውም ደስ ይላቸዋል።
6 ጠባቂዎች፣ በኤፍሬም ኰረብቶች ላይ፣
‘ኑ፤ ወደ ጽዮን፣
ወደ አምላካችን ወደእግዚአብሔርእንውጣ!’
ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣል።
7 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ስለ ያዕቆብ በደስታ ዘምሩ፤
ስለ ሕዝቦች አለቃ እልል በሉ፤
ምስጋናችሁን አሰሙ፤
‘እግዚአብሔርሆይ፤ የእስራኤልን ቅሬታ፣
ሕዝብህን አድን’ በሉ።
8 እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤
ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤
በመካከላቸውም ዕውሮችና አንካሶች፣
ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤
ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።
9 እያለቀሱ ይመጣሉ፤
እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤
እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣
ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣
በውሃ ምንጭ ዳር፣
በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።
10 “ሕዝቦች ሆይ፤የእግዚአብሔርንቃል ስሙ፤
ሩቅ ባሉ የባሕር ጠረፎችም፣
‘እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤
መንጋውንም እንደ እረኛ ይጠብቃል’ ብላችሁ ዐውጁ።
11 እግዚአብሔርያዕቆብን ይዋጀዋልና፤
ከእርሱም ከሚበረቱት እጅ ይታደገዋልና።
12 መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤
በእግዚአብሔርምልግስና፣
በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣
በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤
ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤
ከእንግዲህም አያዝኑም።
13 ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤
ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤
ልቅሶአቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤
ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ።
14 ካህናቱን አትረፍርፌ እባርካለሁ፤
ሕዝቤም በልግስናዬ ይጠግባል፤”
ይላልእግዚአብሔር።
15 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ዋይታና መራራ ልቅሶ፣
ከራማ ተሰማ፤
ልጆቿ የሉምና፣
ራሔል አለቀሰች፤
መጽናናትም እንቢ አለች።”
16 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ድምፅሽን ከልቅሶ፣
ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤
ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤”
ይላልእግዚአብሔር።
“ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
17 ስለዚህ ወደ ፊት ተስፋ አለሽ”
ይላልእግዚአብሔር።
“ልጆችሽ ወደ ገዛ ምድራቸው ይመለሳሉ።
18 “የኤፍሬምን የሲቃ እንጒርጒሮ በእርግጥ ሰምቻለሁ፤
‘እንዳልተገራ ወይፈን ቀጣኸኝ፤
እኔም ተቀጣሁ።
አንተእግዚአብሔርአምላኬ ነህና፣
መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ።
19 ከአንተ ከራቅሁ በኋላ፣
ተመልሼ ተጸጸትሁ፤
ባስተዋልሁም ጊዜ፣
ጭኔን መታሁ፣
የወጣትነት ውርደቴን ተሸክሜአለሁና፣
ዐፈርሁ፤ ቀለልሁም።’
20 ኤፍሬም የምወደው፣
ደስም የምሰኝበት ልጄ አይደለምን?
ብዙ ጊዜ ተቃውሜው ብናገርም፣
መልሼ ስለ እርሱ አስባለሁ፤
አንጀቴ ይላወሳል፤
በታላቅ ርኅራኄም እራራለታለሁ፤”
ይላልእግዚአብሔር።
21 “የጐዳና ምልክት አቁሚ፤
መንገድ አመልካች ትከዪ፤
የምትሄጂበትን መንገድ፣
አውራ ጐዳናውን አስተውዪ፤
ድንግሊቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሺ፤
ወደ ከተሞችሽም ግቢ።
22 አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤
እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ?
እግዚአብሔርበምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤
ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።
23 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ምርኮአቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤እግዚአብሔርይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ።
24 ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ።
25 የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።”
26 በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር።
27 “እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላልእግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤
28 ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላልእግዚአብሔር።
29 “በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣
‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣
የልጆች ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም።
30 ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል።
31 “ከእስራኤል ቤትና፣
ከይሁዳ ቤት ጋር” ይላልእግዚአብሔር፤
“አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት፣
ጊዜ ይመጣል።
32 ከግብፅ አወጣቸው ዘንድ፣
እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣
ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ኪዳን
አይደለም፤
የእነርሱ ባልገ ሆኜ ሳለሁ፣
ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።”
ይላልእግዚአብሔር።
33 “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣
ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላልእግዚአብሔር፤
“ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤
በልባቸውም እጽፈዋለሁ።
እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤
እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።
34 ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣
ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርንዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤
ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣
ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤”
ይላልእግዚአብሔር።
“በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤
ኀጢአታቸውንም መልሼ አላስብም።”
35 በቀን እንድታበራ፣
ፀሓይን የመደበ፣
በሌሊት እንዲያበሩ፣
ጨረቃንና ከዋክብትን ያዘዛቸው፣
የሞገዱ ድምፅ እንዲተምም፣
ባሕሩን የሚያናውጥ፣
ስሙ የሰራዊት ጌታ የሆነ፣
እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
36 “ይህ ሥርዐት በፊቴ ከተሻረ፣”
ይላልእግዚአብሔር፤
“በዚያ ጊዜ የእስራኤልም ዘር በፊቴ፣
መንግሥት መሆኑ ለዘላለም ይቀራል።”
37 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“በላይ ያሉትን ሰማያትን መለካት፣
በታችም ያሉትን የምድር መሠረቶች መመርመር ከተቻለ፣
በዚያ ጊዜ የእስራኤልን ዘር ሁሉ፣
ስላደረጉት ነገር ሁሉ እጥላቸዋለሁ፤”
ይላልእግዚአብሔር።
38 “እነሆ ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ በር ድረስ” ይላልእግዚአብሔር፤“ይህች ከተማለእግዚአብሔርየምትሠራበት ጊዜ ይመጣል፤
39 መለኪያ ገመዱም ከዚያ ጀምሮ በቀጥታ ወደ ጋሬብ ኰረብታ፣ አልፎም ወደ ጎዓ ይዘረጋል።
40 ሬሳና ዐመድ የሚጣልበት ሸለቆ በሙሉ፣ በምሥራቅ በኩል የቄድሮንን ሸለቆ ይዞ እስከ ፈረስ በር የሚደርሰው ደልዳላ ቦታ ሁሉለእግዚአብሔርየተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ከተማይቱ አትነቀልም፤ አትፈርስምም።”