ኤርምያስ 32

ኤርምያስ የዕርሻ ቦታ መግዛቱ

1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፣ ይኸውም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዐሥራ ስምንተኛ ዘመነ መንግሥት፣ከእግዚአብሔርዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤

2 በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምን ከቦ ነበር፤ ነቢዩ ኤርምያስም በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተዘግቶበት ነበር።

3 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም እንዲህ በማለት አሳስሮት ነበር፤ “እንዴት እንደዚህ ያለ ትንቢት ትናገራለህ? ‘እግዚአብሔር፤“ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፎ ይሰጣል፤ ፊት ለፊትም ያነጋግረዋል፤ በዐይኖቹም ያየዋል እንጂ ከባቢሎናውያንእጅ አያመልጥም።

5 ሴዴቅያስንም ወደ ባቢሎን ይወስደዋል፤ በፍርዴ እስከምጐበኘውም ድረስ በዚያ ይቈያል፤ ይላልእግዚአብሔር፤ ከባቢሎናውያን ጋር ብትዋጉ አይሳካላችሁም” ይላል’ ትላለህ።”

6 ኤርምያስምየእግዚአብሔርቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ አለ፦

7 “የአጎትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ፣ ‘የመቤዠት መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በዓናቶት ያለውን መሬቴን ግዛኝ’ ይልሃል።”

8 እግዚአብሔርምእንደ ተናገረኝ፣ የአጎቴ ልጅ አናምኤል ወደ ዘብ ጠባቂዎቹ አደባባይ መጥቶ፣ “የመቤዠቱን ርስት የማድረጉ መብት የአንተ ስለ ሆነ፣ በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን መሬቴን ለራስህ እንዲሆን ግዛው” አለኝ። ይህምየእግዚአብሔርቃል እንደሆነ ዐወቅሁ፤

9 ስለዚህ በዓናቶት ያለውን መሬት ከአጎቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፤ ዐሥራ ሰባት ሰቅልብር መዝኜ ሰጠሁት።

10 በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።

11 የስምምነቱ ዝርዝር ያለበትን፣ የታሸገውንና ያልታሸገውን የግዢውን የውል ሰነድ ወሰድሁ፤

12 በአጎቴም ልጅ በአናምኤልና በውሉ ላይ በፈረሙት ምስክሮች ፊት እንዲሁም በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ ተቀምጠው በነበሩ አይሁድ ሁሉ ፊት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት።

13 በእነርሱ ፊት ለባሮክ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠሁት፤

14 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘የታሸገውንና ያልታሸገውን፣ ሁለቱን የግዢ ውል ሰነዶች ለብዙ ጊዜ ሳይበላሹ እንዲቈዩ ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው።

15 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላልና፤ ሰዎች በዚህ ምድር ቤት፣ የዕርሻ ቦታና የወይን አትክልት ስፍራ እንደ ገና ይገዛሉ።’ ”

16 “ለኔርያ ልጅ ለባሮክ የግዢ ውሉን ከሰጠሁ በኋላ፣ ወደእግዚአብሔርእንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤

17 “አቤት፣ ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም።

18 ፍቅርና ቸርነትን ለእልፍ አእላፍ ታሳያለህ፤ ይሁን እንጂ የአባቶችን በደል ከእነርሱ በኋላ በሚነሡ ልጆቻቸው ጒያ ትመልሳለህ፤ ስምህ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርየሆነ፣ ታላቅና ኀያል አምላክ ሆይ፤

19 ዕቅድህ ታላቅ፣ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ዐይኖችህ የሰው ልጆችን መንገዶች ሁሉ ያያሉ፤ ለእያንዳንዱም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።

20 በግብፅ ታምራትንና ድንቆችን አደረግህ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእስራኤልና በሰው ልጆች ሁሉ መካከል እንደዚያው እያደረግህ ዛሬም ስምህ ገናና ነው።

21 በታምራትና በድንቅ፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ እጅግ በሚያስፈራም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብፅ አወጣህ።

22 ለአባቶቻችን ልትሰጣቸው የማልህላቸውን፣ ማርና ወተት የምታፈሰውን ይህችን ምድር ሰጠሃቸው፤

23 ወደዚያም ገብተው ወረሷት፤ ነገር ግን አልታዘዙህም፤ ሕግህንም አልጠበቁም፤ እንዲያደርጉት ያዘዝሃቸውን ከቶ አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ሁሉ ጥፋት በላያቸው አመጣህ።

24 “እነሆ፤ ከተማዪቱን ለመያዝ የዐፈር ድልድል በዙሪያዋ ተሠርቶአል፤ ከሰይፍ፣ ከራብና ከቸነፈር የተነሣ ከተማዪቱን ለሚወጓት ለባቢሎናውያን ዐልፋ ልትሰጥ ነው፤ እንደምታየውም የተናገርኸው እየተፈጸመ ነው።

25 አንተ ግን ጌታእግዚአብሔርሆይ፤ ከተማዪቱ ለባቢሎናውያን አልፋ እየተሰጠች፣ ‘መሬቱን በብር ግዛ፤ ግዢውንም በምስክሮች ፊት ፈጽም’ ትለኛለህ።”

26 ከዚያም በኋላየእግዚአብሔርቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

27 “እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክእግዚአብሔርነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን?

28 ስለዚህእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ እነሆ፤ ይህቺን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

29 ከተማዪቱን የሚወጓት ባቢሎናውያን ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቡ በየሰገነቱ ላይ ለበኣል ያጠኑባቸውንና ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀረቡባቸውን ቤቶች ጭምር ያነዳሉ።

30 “የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ ከታናሽነታቸው ጀምሮ ከክፉ ነገር በቀር በፊቴ አንዳች በጎ ነገር አልሠሩም፤ በእርግጥም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው ሥራ አስቈጡኝ፤ ይላልእግዚአብሔር።

31 ይህች ከተማ፣ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከፊቴ እንዳስወግዳት ቍጣ ዬንና መዓቴን አነሣሥታለች፤

32 የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብዕጠ እነርሱ፣ ነገሥታታቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸው፣ ካህናታቸው፣ ነቢያታቸው፣ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ባደረጉት ክፋት ሁሉ አስቈጡኝ።

33 ፊታቸውን ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፤ ደጋግሜ ባስተምራቸውም አይሰሙም፤ ተግሣጽም አይቀበሉም።

34 ስሜ በተጠራበት ቤት አስጸያፊ ጣዖታቸውን አቆሙ፤ አረከሱትም።

35 ወንዶችና ሴቶችልጆቻቸውን ለሞሎክ ይሠው ዘንድ በሄኖም ሸለቆ ለበኣል መስገጃ ኰረብቶችን ሠሩ፤ ነገር ግን ይሁዳን ኀጢአት ለማሠራት እንደዚህ ያለውን አስጸያፊ ተግባር እንዲፈጽሙ እኔ አላዘዝሁም፤ ከቶም አላሰብሁም።

36 “ ‘በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር ለባቢሎን ንጉሥ ዐልፋ ትሰጣለች’ ስላልሃት ስለዚህች ከተማ፣ የእስራኤል አምላክእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

37 “በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ በሰላምም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።

38 እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

39 ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ።

40 መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈ ጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።

41 ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ።’ ”

42 “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት እንዳ መጣሁ እንደዚሁ ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ።

43 እናንተም፣ “ለባቢሎናውያን ዐልፋ ስለ ተሰጠች፣ ሰውና እንስሳ የማይኖሩባት ባድማ ናት” ባላችኋት በዚህች ምድር እንደ ገና መሬት ይገዛል።

44 ምርኮአቸውን ስለምመልስላቸውበብንያም አገር፣ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች፣ በይሁዳ ከተሞችና በተራራማው አገር ከተሞች፣ በምዕራብ ተራሮች ግርጌና በኔጌብ ባሉ ከተሞች መሬት በጥሬ ብር ይገዛል፤ ውሉም ተፈርሞ፤ በምስክሮች ፊት ይታሸጋል፤ ይላልእግዚአብሔር።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *