ኤርምያስ 50

ስለ ባቢሎን የተነገረ መልእክት

1 እግዚአብሔርስለ ባቢሎንና ስለ ባቢሎናውያንምድር፣ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል የተናገረው ቃል ይህ ነው፤

2 “በሕዝቦች መካከል ተናገሩ፤ አስታውቁም፤

ሰንደቅ ዐላማ አንሡ፤ ዐውጁ፤

አንዳች ሳታስቀሩ፣ እንዲህ በሉ፤

‘ባቢሎን ትያዛለች፤

ቤል ይዋረዳል፤

ሜሮዳክ በሽብር ይሞላል፤

ጣዖቶቿ ይዋረዳሉ፤

አማልክቷም ይሸበራሉ።’

3 ከሰሜን አንድ መንግሥት መጥቶ ይወጋታል፤

ምድሯንም ባድማ ያደርጋል፤

የሚኖርባትም አይገኝም፤

ሰዎችና እንስሳትም ሸሽተው ይሄዳሉ።

4 “በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜም፤”

ይላልእግዚአብሔር፤

“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ በአንድነት ይመጣሉ፤

አምላካቸውንምእግዚአብሔርንበመፈለግ እያለቀሱ ይመጣሉ።

5 ወደ ጽዮን የሚወስደውን መንገድ ይጠይቃሉ፤

ፊታቸውንም ወደዚያ ያቀናሉ።

መጥተውም ከቶ በማይረሳ፣

በዘላለም ቃል ኪዳን፣

ከእግዚአብሔርጋር ይጣበቃሉ።

6 “ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤

እረኞቻቸው አሳቷቸው፤

በተራሮችም ላይ እንዲቅበዘበዙ አደረጓቸው፤

በተራራና በኰረብታ ላይ ተንከራተቱ፤

ማደሪያቸውንም ረሱ።

7 ያገኛቸው ሁሉ ይውጣቸዋል፤

ጠላቶቻቸውም፣ ‘እኛ በደለኞች አይደለንም፤

እነርሱ የአባቶቻቸውን ተስፋ እግዚአብሔርን፣

እውነተኛ ማደሪያቸው የሆነውንእግዚአብሔርንበድለዋል’ አሉ።

8 “ከባቢሎን ሽሹ፤

የባቢሎናውያንን ምድር ልቀቁ፤

መንጋ እንደሚመራ የፍየል አውራ ሁኑ።

9 የታላላቅ መንግሥታትን ማኅበር፣

ከሰሜን በባቢሎን ላይ አስነሣለሁ፤

እነርሱም በእርሷ ላይ ይሰለፋሉ፤

መጥተውም ይይዟታል።

ቀስቶቻቸው ባዶ እጃቸውን እንደ ማይመለሱ፣

እንደ ሥልጡን ተዋጊዎች ናቸው።

10 የባቢሎን ምድርትዘረፋለች፤

የሚዘርፏትም ሁሉ እስኪበቃቸው ይመዘብሩአታል፤”

ይላልእግዚአብሔር።

11 “እናንተ ርስቴን የበዘበዛችሁ ሆይ፤

ደስ ስላላችሁና ሐሤትም ስላደረጋችሁ፣

በመስክ እንዳለች ጊደር ስለ ፈነጫችሁ፤

እንደ ድንጒላ ፈረስ ስለ አሽካካችሁ፤

12 እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፤

የወለደቻችሁም ትዋረዳለች።

እርሷም ምድረ በዳ፣ ደረቅ ምድርና በረሓ፣

ከመንግሥታትም ሁሉ ያነሰች ትሆናለች።

13 ከእግዚአብሔርቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ፣

የሚኖርባት አይገኝም፤

በቍስሎችዋም ሁሉ ምክንያት፣

በባቢሎን የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ ያፌዝባታልም።

14 “እናንተ ቀስት የምትገትሩ ሁሉ፣

በባቢሎን ዙሪያ ተሰለፉ፤

አንዳች ሳታስቀሩ ፍላጾችን ስደዱባት፤

በእግዚአብሔርላይ ኀጢአት ሠርታለችና።

15 ከየአቅጣጫው ጩኹባት፤

እጇን ትሰጣለች፤ ምሽጓም ይወድቃል፤

ቅጥሮቿ ይፈርሳሉ።

ይህየእግዚአብሔርበቀል ነውና፣

እርሷን ተበቀሏት፤

በሌሎቹ ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።

16 ከባቢሎን ዘር የሚዘራውን፣

በመከር ጊዜ ማጭድ የጨበጠውንም ዐጫጅ አጥፉት፤

ከአጥፊው ሰይፍ የተነሣ፣

እያንዳንዱ ወደ ገዛ ሕዝቡ ይመለስ፤

ወደ ገዛ ምድሩም ይሽሽ።

17 “እስራኤል አንበሶች ያሳደዱት፣

የተበተነ መንጋ ነው፤

መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ፣

ቦጫጭቆ በላው፤

በኋላም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣

አጥንቱን ቈረጣጠመው።”

18 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁት ሁሉ፣

የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ።

19 እስራኤልንም ወደ መሰማሪያው እመልሰዋለሁ፤

በቀርሜሎስና በባሳን ላይ ይሰማራል፤

በኤፍሬም ተራሮችና በገለዓድም ላይ፣

እስኪጠግብ ይመገባል።

20 በእነዚያ ጊዜያት፣ በዚያ ዘመን፣”

ይላልእግዚአብሔር፤

“የእስራኤል በደል ይፈለጋል፤

አንዳችም አይገኝም፤

የይሁዳም ኀጢአት ይፈለጋል፤

ከቶም የለም፤

እንዲተርፉ ያደረግኋቸውን ትሩፋን እምራለሁና።

21 “የምራታይምን ምድር፣

የፋቁድ ነዋሪዎችንም፣

አሳዷቸው፤ ግደሏቸው፤ ፈጽማችሁም አጥፏቸው፤”

ይላልእግዚአብሔር፤

“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ።

22 በምድሪቱ የጦርነት ውካታ፣

የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰማ።

23 የምድር ሁሉ መዶሻ፣

እንዴት ተሰበረ! እንዴትስ ደቀቀ!

በሕዝቦች መካከል፣

ባቢሎን እንዴት ባድማ ሆነች!

24 ባቢሎን ሆይ፤ ወጥመድ ዘርግቼልሻለሁ፤

አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤

እግዚአብሔርንተገዳድረሻልና፣

ተገኘሽ፤ ተያዝሽም።

25 እግዚአብሔርየመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ከፍቶአል፤

የቍጣውን የጦር ዕቃ አውጥቶአል፤

የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣

በባቢሎናውያን ምድር ሥራ አለውና።

26 ከሩቅ መጥታችሁ በእርሷ ላይ ውጡ፤

ጐተራዎቿን አፈራርሱ፤

እንደ እህል ክምር ከምሯት፤

ፈጽማችሁ አጥፏት፤

ምኗም አይቅር።

27 ወይፈኖቿን ሁሉ ዕረዱ፤

ወደ መታረጃም ይውረዱ!

የሚቀጡበት ጊዜ፣

ቀናቸው ደርሶአልና ወዮላቸው!

28 እግዚአብሔርአምላካችን የተበቀለውን፣

ስለ ቤተ መቅደሱ የተበቀለውን በቀል፣

ከባቢሎን የመጡ ኰብላዮችና ስደተኞች፣

በጽዮን የሚናገሩትን ስሟቸው።

29 “ቀስት የሚገትሩትን፣

ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩ፤

አንድም ሰው እንዳያመልጥ፣

ዙሪያውን ሁሉ መሽጉ፤

የእስራኤልን ቅዱስ፣

እግዚአብሔርንአቃላለችና፣

እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፤

በሌሎች ላይ እንዳደረገችውም አድርጉባት።

30 ስለዚህ ወንዶች ወጣቶቿ በየአደባባዩ ይረግፋሉ፤

በዚያ ቀን ወታደሮቿ ሁሉ ይወድቃሉ፤”

ይላልእግዚአብሔር፤

31 “አንተ ትዕቢተኛ፤ እነሆ፣ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤”

ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፤

“የምትቀጣበት ጊዜ፣

ቀንህ ደርሶአልና።

32 ትዕቢተኛው ይሰናከላል፤ ይወድቃልም፤

የሚያነሣውም የለም፤

በዙሪያው ያሉትን ሁሉ የሚበላ እሳት፣

በከተሞቹ ውስጥ አስነሣለሁ።”

33 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“የእስራኤል ሕዝብና የይሁዳ ሕዝብ፣

በአንድነት ተጨቍነዋል፤

የማረኳቸውም ሁሉ አጥብቀው ይዘዋቸዋል፤

ይለቅቋቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል።

34 ነገር ግን ቤዛቸው ብርቱ ነው፤

ስሙም የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርነው፤

ለምድራቸው ዕረፍትን ለመስጠት፤

ተግቶ ይሟገትላቸዋል፤

በባቢሎን የሚኖሩትን ግን ዕረፍት ይነሣቸዋል።

35 “ሰይፍ በባቢሎናውያን ላይ መጣ!”

ይላልእግዚአብሔር፤

“በባቢሎን ነዋሪዎች ላይ፤

በባለ ሥልጣኖቿና በጥበበኞቿም ላይ ተመዘዘ!

36 ሰይፍ በሐሰተኞች ነቢያቷ ላይ መጣ!

እነርሱም ሞኞች ይሆናሉ፤

ሰይፍ በጦረኞቿ ላይ ተመዘዘ፤

እነርሱም ይሸበራሉ።

37 ሰይፍ በፈረሰኞቿና በሠረገሎቿ ላይ፣

በመካከሏ ባሉት ባዕዳን ወታደሮች ሁሉ ላይ መጣ!

እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤

ሰይፍ በሀብት ንብረቷ ላይ መጣ!

ለዝርፊያም ይሆናሉ።

38 ድርቅበውሆቿ ላይ መጣ!

እነሆ፤ ይደርቃሉ፤

ምድሪቱ በፍርሀት በሚሸበሩ አማልክት፣

በጣዖትም ብዛት ተሞልታለችና።

39 “ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊትና የጅብ መኖሪያ፣

የጒጒትም ማደሪያ ትሆናለች፤

ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አይኖርባትም፤

ከትውልድ እስከ ትውልድም የሚቀመጥባት አይገኝም።

40 እግዚአብሔርሰዶምንና ገሞራን፤

በዙሪያቸውም የነበሩትን ከተሞች ያለ ነዋሪ እንዳስቀራቸው”

ይላልእግዚአብሔር፤

“እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፣

የሚቀመጥባትም አይገኝም።

41 “እነሆ፤ ሰራዊት ከሰሜን ይመጣል፤

አንድ ኀያል መንግሥትና ብዙ ነገሥታት፣

ከምድር ዳርቻ ተነሣሥተዋል።

42 ቀስትና ጦር ይዘዋል፤

ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም አያደርጉም፤

በፈረሳቸው እየጋለቡ ሲመጡ፣

ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይተማል፤ ያስገመግማል።

አንቺ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፤

ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ተዋጊዎች ይመጡብሻል።

43 የባቢሎን ንጉሥ ስለ እነርሱ ሰማ፤

እጆቹም በድን ሆኑ፤

ጭንቀት ይዞታል፤

ምጥ እንደ ያዛት ሴት ታሟል።

44 አንበሳ ከዮርዳኖስ ደኖች ድንገት ወጥቶ፣

ወደ ግጦሽ ሜዳ ብቅ እንደሚል፣

እኔም ባቢሎንን ሳይታሰብ ከምድሯ አባርራታለሁ፤

የመረጥሁትንም በእርሷ ላይ እሾማለሁ፤

እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊገዳደረኝ ይችላል?

የትኛውስ እረኛ ሊቋቋመኝ ይችላል?

45 ስለዚህእግዚአብሔርበባቢሎን ላይ ያቀደውን፣

በባቢሎናውያንም ምድር ላይ ያሰበውን ስሙ፤

ከመንጋው ታናናሹ ተጐትቶ ይወሰዳል፤

በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸውን ፈጽሞ ያጠፋል።

46 በባቢሎን ውድቀት ድምፅ ትናወጣለች፤

ጩኸቷም በሕዝቦች መካከል ያስተጋባል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *