ኤርምያስ 51

1 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ በባቢሎንናበምድሯ ላይ፣

የሚያጠፋ ነፋስ አስነሣለሁ።

2 እንዲያበጥሯትና እንዲያወድሟት፣

ባዕዳንን በባቢሎን ላይ እልካለሁ፤

በመከራዋም ቀን፣

ከበው ያስጨንቋታል።

3 ቀስተኛው ቀስቱን እስኪገትር፣

የጦር ልብሱንም እስኪለብስ ፋታ አትስጡት፤

ለወጣቶቿ አትዘኑ፤

ሰራዊቷንም ፈጽማችሁ አጥፉ።

4 በባቢሎንምድር ታርደው፣

በአደባባዮቿም እስከ ሞት ቈስለው ይወድቃሉ።

5 ምድራቸውበእስራኤል ቅዱስ ፊት፣

በበደል የተሞላች ብትሆንም፣

እስራኤልንና ይሁዳን አምላካቸው፣

የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርአልጣላቸውም።

6 “ከባቢሎን ሸሽታችሁ ውጡ

ፈጥናችሁም ሕይወታችሁን አትርፉ!

በኀጢአቷ ምክንያት አትጥፉ።

የእግዚአብሔርየበቀል ጊዜ ነው፤

እርሱም የሥራዋን ይከፍላታል።

7 ባቢሎንበእግዚአብሔርእጅ የወርቅ ጽዋ ነበረች፤

ምድርንም ሁሉ አሰከረች።

ሕዝቦች ከወይን ጠጇ ጠጡ፤

ስለዚህ አሁን አብደዋል።

8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ትሰበራለች፤

ዋይ በሉላት!

ምናልባት ልትፈወስ ስለምትችል፣

ለቍስሏ የሚቀባ መድኀኒት ፈልጉላት።

9 “ ‘ባቢሎንን ለመፈወስ ሞክረን ነበር፤

እርሷ ግን ልትፈወስ አትችልም፤

ፍርዷ እስከ ሰማይ ስለ ደረሰ፣

እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ስላለ፣

ትተናት ወደየአገራችን እንሂድ።’

10 “ ‘እግዚአብሔርቅንነታችንን መሰከረ፤

ኑ፤ አምላካችንእግዚአብሔርያደረገውን፣

በጽዮን እንናገር።’

11 “ፍላጾችን ሳሉ፤

ጋሻዎችን አዘጋጁ፤

የእግዚአብሔርሐሳብ ባቢሎንን ለማጥፋት ስለ ሆነ፣

የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቶአል፤

እግዚአብሔርይበቀላል፤

ስለ ቤተ መቅደሱ ይበቀላል።

12 በባቢሎን ቅጥር ላይ ዐላማ አንሡ

ጥበቃውን አጠናክሩ፤

ዘብ ጠባቂዎችን አቁሙ፤

ደፈጣ ተዋጊዎችን አዘጋጁ

እግዚአብሔርበባቢሎን ሕዝብ ላይ የወሰነውን፣

ዐላማውን ያከናውናል።

13 አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣

በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤

የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቶአል፤

ፍጻሜሽ ደርሶአል።

14 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል፤

ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሰራዊት ያጥለቀልቅሻል፤

እነርሱም በድል አድራጊነት በላይሽ ያቅራራሉ።

15 “ምድርን በኀይሉ የሠራ፣

ዓለምን በጥበቡ የመሠረተ፣

ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው።

16 ድምፁን ባንጐደጐደ ጊዜ በሰማይ ውሆች ይናወጣሉ፤

ጉሙን ከምድር ዳርቻ ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤

መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤

ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

17 “እያንዳንዱ ሰው ጅልና ዕውቀት የለሽ ነው፤

የወርቅ አንጥረኛው ሁሉ በሠራው በጣዖቱ ዐፍሮአል፤

የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤

እስትንፋስ የላቸውም።

18 እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፣

ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።

19 የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደ እነዚህ አይደለም፤

እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤

እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።

ስሙ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርነው።

20 “አንቺ የእኔ ቈመጥ፣

የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤

በአንቺ ሕዝቦችን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ መንግሥታትን አጠፋለሁ፤

21 በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ሠረገላውንና ሠረገላ ነጂውን እሰባብራለሁ፤

22 በአንቺ ወንዱንና ሴቱን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ሽማግሌውንና ወጣቱን እሰባብራለሁ።

በአንቺ ጐረምሳውንና ኰረዳዪቱን እሰባብራለሁ።

23 በአንቺ እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፣

በአንቺ ገበሬውንና በሬውን እሰባብራለሁ፤

በአንቺ ገዦችንና ባለ ሥልጣኖችን እሰባብራለሁ።

24 “በጽዮን ላይ ስላደረሱት ጥፋት ሁሉ ለባቢሎንና በባቢሎንለሚኖሩት ሁሉ ዐይናችሁ እያየ ዋጋቸውን እከፍላቸዋለሁ” ይላልእግዚአብሔር።

25 “አንቺ ምድርን ሁሉ ያጠፋሽ፣

አጥፊ ተራራ ሆይ፤ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣”

ይላልእግዚአብሔር፤

“እጄን በአንቺ ላይ አነሣለሁ፤

ከገመገም ቍልቍል አንከባልልሻለሁ፤

የተቃጠለም ተራራ አደርግሻለሁ።

26 ከአንቺ ለማእዘን የሚሆን ድንጋይ፣

ለመሠረትም የሚሆን ዐለት አይወሰድም፤

ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ፤”

ይላልእግዚአብሔር።

27 “በምድር ሁሉ ላይ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ!

በሕዝቦች መካከል መለከትን ንፉ!

ሕዝቦችን ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤

የአራራትን፣ የሚኒንና የአስከናዝን መንግሥታት፣

ጠርታችሁ በእርሷ ሰብስቡአቸው፤

የጦር አዝማች ሹሙባት፤

ፈረሶችንም እንደ አንበጣ መንጋ ስደዱባት።

28 የሜዶንን ነገሥታት፣

ገዦቿንና ባለሥልጣኖቿን ሁሉ፣

በግዛታቸው ሥር ያሉትን አገሮች ሁሉ፣

እነዚህን ሕዝቦች ለጦርነት አዘጋጁባት።

29 ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣

የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣

እግዚአብሔርበባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣

ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።

30 የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤

በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤

ኀይላቸው ተሟጦአል፤

እንደ ሴት ሆነዋል፤

በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሶአል፤

የደጇም መወርወሪያ ተሰብሮአል።

31 ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ መያዟን፣

ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር፣

አንዱ ወሬኛ ሌላውን ወሬኛ፣

አንዱ መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ወዲያው ወዲያው ይከተላል፤

32 መልካዎቿ እንደተያዙ፣

የወንዝ ዳር ምሽጎቿ እንደ ተቃጠሉ፣

ወታደሮቿም እንደ ተደናገጡ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።”

33 የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣

የእህል መውቂያ አውድማ ናት፤

የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።

34 “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላን፣

አድቅቆ ፈጨን፤

እንደ ባዶ ማድጋ አደረገን፤

እንደ ዘንዶ ዋጠን፣

እንደ ጣፋጭ በልቶን ሆዱን ሞላ፤

በኋላም አንቅሮ ተፋን፤

35 የጽዮን ነዋሪዎች፣ እንዲህ ይላሉ፤

“በሥጋችንላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን፤”

ኢየሩሳሌም እንዲህ ትላለች፤

“ደማችን በባቢሎን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን።”

36 ስለዚህእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ እሟገትልሻለሁ፣

በቀልሽንም እኔ እበቀልልሻለሁ፤

ባሕሯን አደርቃለሁ፣

የምንጮቿንም ውሃ።

37 ባቢሎን የፍርስራሽ ክምር፣

የቀበሮዎች መፈንጫ፣

የድንጋጤና የመሣለቂያ ምልክት ትሆናለች፤

የሚኖርባትም አይገኝም።

38 ሕዝቦቿ ሁሉ እንደ ደቦል አንበሳ ያገሣሉ፤

እንደ አንበሳ ግልገልም ያጒረመርማሉ።

ጒሮሮአቸው በደረቀ ጊዜ

ድግስ አዘጋጅላቸዋለሁ፤

እንዲሰክሩም አደርጋቸውና፤”

39 በሣቅ እየፈነደቁ፣

ለዘላለም ላይነቁ ይተኛሉ።”

ይላልእግዚአብሔር።

40 “እንደ ጠቦት፣

እንደ አውራ በግና እንደ ፍየል፣

ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ።

41 “ሼሻክእንዴት ተማረከች!

የምድር ሁሉ ትምክህትስ እንዴት ተያዘች!

ባቢሎን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ፣

ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች።

42 ባሕር በባቢሎን ላይ ይወጣል፤

ሞገዱም እየተመመ ይሸፍናታል።

43 ከተሞቿ ሰው የማይኖርባቸው፣

ዝርም የማይልባቸው፣

ደረቅና በረሓማ ቦታ፣

ባድማ ምድርም ይሆናሉ።

44 ቤልን በባቢሎን ውስጥ እቀጣለሁ፤

የዋጠውን አስተፋዋለሁ፤

ሕዝቦች ከእንግዲህ ወደ እርሱ አይጐርፉም፤

የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል።

45 “ሕዝቤ ሆይ፤ ከመካከሏ ውጡ

ሕይወታችሁን አትርፉ!

ከአስፈሪውየእግዚአብሔርቍጣ አምልጡ።

46 ወሬ በምድሪቱ ሲሰማ፣

ተስፋ አትቍረጡ፤ አትፍሩም፤

ገዥ በገዥ ላይ ስለ መነሣቱ፣

ዐመፅም በምድሪቱ ስለ መኖሩ፣

አንድ ወሬ ዘንድሮ፣ ሌላውም ለከርሞ ይመጣል፤

47 የባቢሎንን ጣዖታት የምቀጣበት ጊዜ፣

በርግጥ ይመጣልና።

ምድሯ በሙሉ ትዋረዳለች፤

የታረዱትም በሙሉ በውስጧ ይወድቃሉ።

48 ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ፣

በባቢሎን ላይ እልል ይላሉ፤

አጥፊዎች ከሰሜን ወጥተው፣

እርሷን ይወጓታልና፤”

ይላልእግዚአብሔር።

49 “በምድር ሁሉ የታረዱት፣

በባቢሎን ምክንያት እንደ ወደቁ፣

ባቢሎንም በእስራኤል በታረዱት ምክንያት መውደቅ ይገባታል።

50 ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፤

ሂዱ! ጊዜ አትፍጁ፤

በሩቅ ምድር ያላችሁእግዚአብሔርንአስታውሱ፤

ኢየሩሳሌምንም አስቧት።”

51 “ባዕዳን ሰዎች ወደ ተቀደሰው፣

ወደእግዚአብሔርቤት ስለ ገቡ፣

እኛ ተሰድበናል፤

ዕፍረትም ፊታችንን ሸፍኖአል፤

ውርደትም ተከናንበናል።”

52 “እንግዲህ ጣዖቶቿን የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፤”

ይላልእግዚአብሔር፤

“በምድሯም ሁሉ፤

ቍስለኞች ያቃስታሉ።

53 ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣም፣

ከፍ ያለ ምሽጓን ብታጠናክርም፣

አጥፊዎች እሰድባታለሁ፤”

ይላልእግዚአብሔር።

54 “ከባቢሎን ጩኸት፣

ከባቢሎናውያንምየምድር፣

የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል።

55 እግዚአብሔርባቢሎንን ያጠፋታል፤

ታላቅ ጩኸቷንም ጸጥ ያደርጋል።

ሞገዳቸው እንደ ታላቅ ውሃ ይተማል፤

ጩኸታቸውም ያስተጋባል።

56 በባቢሎን ላይ አጥፊ ይመጣል፤

ጦረኞቿ ይማረካሉ፤

ቀስታቸውም ይሰበራል፤

እግዚአብሔርግፍን የሚበቀል፣

ተገቢውንም ሁሉ የሚከፍል አምላክ ነውና።

57 ባለ ሥልጣኖቿንና ጥበበኞቿን፣

ገዦቿንና መኳንንቷን፣ ጦረኞቿንም አሰክራለሁ፤

ለዘላለም ይተኛሉ፤ አይነቁምም፤”

ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ

እግዚአብሔርየሆነው ንጉሥ።

58 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤

“ወፍራሙ የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል፤

ከፍ ያሉት ደጆቿም በእሳት ይቃጠላሉ፤

ሰዎቹ በከንቱ ይደክማሉ፤

የሕዝቡም ልፋት ለእሳት ይሆናል።”

59 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የንጉሡ የግቢ አስከልካይ የነበረው የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ ከንጉሡ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ የሰጠው መልእክት ይህ ነው።

60 ኤርምያስ ስለ ባቢሎን ጽፎ ያስቀመጠውን ሁሉ፣ በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት ሁሉ በብራና ጥቅልል ላይ ጻፈው፤

61 ለሠራያም እንዲህ አለው፤ “ባቢሎን በደረስህ ጊዜ፣ ይህን ቃል ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብ አትዘንጋ

62 እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔርሆይ፤ ይህችን ስፍራ ሰውም ሆነ እንስሳ እስከማይኖርባት ድረስ ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ ብለሃል።’

63 ይህን ብራና አንብበህ ከጨረስህ በኋላ፣ ድንጋይ አስረህበት ኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ጣለው፤

64 እንዲህም በል፤ ‘ባቢሎንም እኔ ከማመጣባት ጥፋት የተነሣ፣ እንደዚሁ ትሰጥማለች፤ ከእንግዲህም አትነሣም፤ ሕዝቧም ይወድቃል።’ ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *