1 “ ‘በዚያን ጊዜ፣ ይላልእግዚአብሔር፤ የይሁዳን ነገሥታትና መኳንንት ዐፅም፣ የካህናትና የነቢያት ዐፅም፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዐፅም ከየመቃብራቸው ይወጣል።
2 በወደዷቸውና በአገለገሏቸው እንዲሁም በተከተሏቸው፣ ባማከሯቸውና ባመለኳቸው በፀሓይ፣ በጨረቃና በሰማያት ከዋክብት ሁሉ ፊት ይሰጣል፤ አይሰበሰብም ወይም አይቀበርም፤ ነገር ግን እንደተጣለ ጒድፍ በምድር ላይ ይበተናል።
3 ከዚህ ክፉ ሕዝብ የተረፉት ሁሉ፣ ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ፤ ይላል የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር።’
ኀጢአትና ያስከተለው ቅጣት
4 “እንዲህ በላቸው፤እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ ‘ሰዎች ቢውድቁ፣ እንደ ገና ከወደቁበት አይነሡምን?
ሰው ተሳስቶ ወደ ኋላ ቢሄድ፣ ከስሕተቱ አይመለስምን?
5 ታዲያ፣ ይህ ሕዝብ ለምን ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ይሄዳል?
ለምንስ ኢየሩሳሌም ዘወትር ወደ ኋላ ትመለሳለች?
ተንኰልን የሙጥኝ ብለው ይዘዋል፤
ሊመለሱም ፈቃደኛ አይደሉም።
6 እኔ በጥንቃቄ አደመጥኋቸው፤
ትክክለኛ የሆነውን ግን አይናገሩም።
ማንም ስለ ክፋቱ ንስሓ የገባ የለም፤
“ምን አድርጌአለሁ?” ይላል።
ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ፈረስ፣
እያንዳንዱ በራሱ መንገድ ይሄዳል።
7 ሽመላ እንኳ በሰማይ፣
የተወሰነ ጊዜዋን ታውቃለች፣
ዋኖስ፣ ጨረባና ዋርዳም፣
የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤
ሕዝቤ ግን፣
የእግዚአብሔርንሥርዐት አላወቀም።
8 “ ‘የጸሓፊዎቻችሁ ሐሰተኛ ብርዕ ሐሰት
እያስተናገደ እንዴት፣ “ዐዋቂዎች ነን፣
የእግዚአብሔርሕግ አለን” ትላላችሁ?
9 ጥበበኞች ያፍራሉ፤
ይዋረዳሉ፤ በወጥመድም ይያዛሉ።
የእግዚአብሔርንቃል ተቃውመው፣
ምን ዐይነት ጥበብ ይኖራቸዋል?
10 ስለዚህ ሚስቶቻቸውንም ለሌሎች ወንዶች እሰጣለሁ፤
ዕርሻዎቻቸውንም ለባዕዳን እሰጣለሁ፤
ከታናሹ እስከ ታላቁ ድረስ፣
ሁሉም ተገቢ ላልሆነ ጥቅም ይስገበገባሉ፤
ነቢያትና ካህናትም እንዲሁ፤
ሁሉም ያጭበረብራሉ።
11 የሕዝቤን ቍስል ብርቱ እንዳይደለ በመቍጠር፣
የተሟላ ፈውስ ሳይኖር እንዲሁ ያክማሉ፤
ሰላም ሳይኖር፣
“ሰላም፣ ሰላም” ይላሉ።
12 ርኵሰት ሲፈጽሙ ዐፍረው ነበርን?
የለም! በጭራሽ አላፈሩም፤
ኀፍረት ምን እንደሆነም አያውቁም።
ስለዚህ ከወደቁት ጋር ይወድቃሉ፤
በምቀጣቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፤”
ይላልእግዚአብሔር።
13 “ ‘ያመረቱትን ሁሉ እወስድባቸዋለሁ፤
ይላልእግዚአብሔር፤
በወይን ተክል ላይ የወይን ፍሬ አይኖርም፤
በበለስ ዛፍ ላይ የበለስ ፍሬ አይገኝም፤
ቅጠሎቻቸውም ይረግፋሉ።
የሰጠኋቸው በሙሉ፣
ከእነርሱ ይወሰድባቸዋል።’ ”
14 “ለምን እዚህ እንቀመጣለን?
በአንድነት ተሰብሰቡ!
ወደ ተመሸጉት ከተሞች እንሽሽ፤
በዚያም እንጥፋ!
በእርሱ ላይ ኀጢአትን ስላደረግን፣
እግዚአብሔርአምላካችን እንድንጠፋ አድርጎናል፤
የተመረዘ ውሃ እንድንጠጣ ሰጥቶናል።
15 ሰላምን ተስፋ አደረግን፤
መልካም ነገር ግን አልመጣም፤
የፈውስ ጊዜን ተመኘን፤
ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነብን።
16 የጠላት ፈረሶች ፉርፉርታ፣
ከዳን ይሰማል፤
በድንጒላ ፈረሶቻቸው ማሽካካት፣
መላዋ ምድር ተንቀጠቀጠች።
ምድሪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣
ከተማዪቱንና በውስጧ የሚኖሩትን ሁሉ፣
ሊውጡ መጡ።”
17 “እነሆ፤ በመካከላችሁ መርዘኛ እባቦችን፣
የአስማተኛ ብልኀት የማይገታቸው እፉኝቶችን እሰዳለሁ፤
እነርሱም ይነድፉአችኋል፤”
ይላልእግዚአብሔር።
18 በሐዘኔ የምታጽናናኝሆይ፤
ልቤ በውስጤ ዝላለች።
19 እንዲህ የሚለውን የሕዝቤን ጩኸት፣
ከሩቅ ምድር ስማ፦
እግዚአብሔርበጽዮን የለምን?
ንጉሥዋስ በዚያ አይኖርምን?”
“በተቀረጹ ምስሎቻቸው፣
እንዲሁም ከንቱ በሆኑ ባዕዳን ለምን አስቈጡኝ?”
20 “መከሩ ዐለፈ፤
በጋው አበቃ፤
እኛም አልዳንም።”
21 ሕዝቤ ሲቈስል፣
እኔም ቈሰልሁ፤
አለቀስሁ፤ ድንጋጤ ያዘኝ።
22 በገለዓድ የሚቀባ መድኀኒት የለምን?
ወይስ በዚያ ሐኪም አልነበረምን?
ለሕዝቤ ቍስል፣
ለምን ፈውስ አልተገኘም?