1 ስለ ታረዱት ወገኖቼ፣
ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፣
ምነው፣ ራሴ የውሃ ምንጭ በሆነ!
ምነው ዐይኖቼ የእንባ መጒረፊያ በሆኑልኝ!
2 ሕዝቤን ትቼ፣ ርቄ እንድሄድ፣
በምድረ በዳ የእንግዶች ማደሪያ ማን በሰጠኝ!
ሁሉም አመንዝሮች፣
የአታላዮች መንጋ ሆነዋላ!
3 “ሐሰትን ለመናገር፣
ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤
በእውነት ሳይሆን፣
በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤
ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤
እኔንም አላወቁኝም፤”
ይላልእግዚአብሔር።
4 “እያንዳንዱ ወንድም አታላይ፣
ባልንጀራም ሁሉ ሐሜተኛ ስለ ሆነ፣
ወንድም ከወንድሙ፣ ይጠንቀቅ፣
ባልንጀራም በጓደኛው አይታመን።
5 ባልንጀራ ባልንጀራውን ያታልላል፤
እውነትን የሚናገር የለም፤
ሐሰትን ይናገር ዘንድ ምላሳቸውን አሠልጥነዋል፤
ኀጢአትንም በማድረግ ራሳቸውን አድክመዋል።
6 መኖሪያህበሽንገላ መካከል ነው፤
ከሽንገላቸውም የተነሣ ሊያውቁኝ አልፈቀዱም፤”
ይላልእግዚአብሔር።
7 ስለዚህ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ እንደ ብረት አነጥራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁም፤
ስለ ሕዝቤ ኀጢአት፣
ከዚህ የተለየ ምን ማድረግ እችላለሁ?
8 ምላሳቸው የሚገድል ቀስት ነው፤
በሽንገላ ይናገራል፤
ሁሉም ከባልንጀራው ጋር በፍቅር ይናገራል፤
በልቡ ግን ያደባበታል።
9 ታዲያ ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?”
ይላልእግዚአብሔር፤
“እንደዚህ ዐይነቱንስ ሕዝብ፣
አልበቀልምን?
10 ስለ ተራሮች አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይ እላለሁ፤
በምድረ በዳ ስላሉትም መሰማሪያዎች አዝናለሁ፤
ሰው የማያልፍባቸው ባድማ ሆነዋል፤
የከብቶች ጩኸት አይሰማም፤
የሰማይ ወፎች ሸሽተዋል፤
የዱር አራዊትም ጠፍተዋል።
11 “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣
የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤
የይሁዳንም ከተሞች፣
ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
12 ይህን መረዳት የሚችል ጥበበኛ ሰው ማን ነው?እግዚአብሔርገልጾለት ይህንስ ማስረዳት የሚችል ማን ነው? ምድሪቱስ ሰው እንደማያልፍበት በረሓ ለምን ጠፋች? ለምን ወና ሆነች?
13 እግዚአብሔርምእንዲህ አለ፤ “ይህ የሆነው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተው ስላልታዘዙኝና ሥርዐቴን ስላልተከተሉ ነው።
14 በዚህ ፈንታ፣ በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን በአሊምን ተከተሉ።”
15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታእግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ይህን ሕዝብ መራራ ምግብ አበላዋለሁ፤ የተመረዘንም ውሃ አጠጣዋለሁ።
16 እነርሱንም ሆነ አባቶቻቸውን በማያውቋቸው ሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።”
17 የሰራዊት ጌታእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“እንግዲህ፤ አልቃሽ ሴቶች ጥሩ፤
ሥልጡን ሙሾ አውራጆች አስመጡ፤
18 እነርሱ ፈጥነው ይምጡ፤
ዐይኖቻችን እንባ እስኪያጐርፉ፣
ሽፋሽፍቶቻችንም ውሃ እስኪያመነጩ፣
ስለ እኛ ሙሾ ያውርዱልን።
19 እነሆ የዋይታ ድምፅ ከጽዮን ተሰምቶአል፤ እንዲህም ይላል፤
‘ምንኛ ወደቅን!
ውርደታችንስ እንዴት ታላቅ ነው!
ቤቶቻችን ፈራርሰዋልና፤
አገራችንን ጥለን እንሂድ።’ ”
20 እናንት ሴቶች ሆይ፤የእግዚአብሔርንቃል ስሙ፤
ጆሮቻችሁን ከአንደበቱ ለሚወጡት ቃላት ክፈቱ፤
ሴቶች ልጆቻችሁን ዋይታ፣
አንዳችሁም ሌላውን ሙሾ አስተምሩ።
21 ሞት በመስኮቶቻችን ገብቶአል፤
ወደ ምሽጎቻችንም ዘልቆአል፤
ሕፃናትን ከየመንገዱ፣
ወጣቶችን ከየአደባባዩ ጠራርጎ ወስዶአል።
22 እንዲህ በሉ፤ “እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ ‘የሰዎች ሬሳ፣
በሜዳ እንደተጣለ ጒድፍ፣
ማንም እንደማይሰበስበው፣
ከዐጫጅ ኋላ እንደተተወ ቃርሚያ ይወድቃል።’ ”
23 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤
“ጥበበኛ በጥበቡ አይታበይ፤
ኀያልም በኀይሉ አይመካ፤
ሀብታምም በሀብቱ አይኵራራ፤
24 የሚመካ ግን፣
እኔእግዚአብሔርእንደሆንሁ በማወቁና፣
በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣
በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣
እደሰታለሁና፤”
ይላልእግዚአብሔር።
25 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “ሥጋቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤
26 እነርሱም ግብፅ፣ ይሁዳ፣ ኤዶም፣ አሞን፣ ሞዓብና ጠጒራቸው ዙሪያውን የሚከረከም የበረሓነዋሪዎች ሁሉ ናቸው፤ እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ በርግጥ የተገረዙ አይደሉምና፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው አልተገረዘም።