1 ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር፤
የዕንባቆም ማጒረምረም
2 እግዚአብሔርሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣
አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?
“ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣
አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?
3 ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ?
እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?
ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤
ጠብና ግጭት በዝቶአል።
4 ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፤
ፍትሕ ድል አይነሣም፤
ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣
ክፉዎች ጻድቃንን ይከባሉ።
የእግዚአብሔር መልስ
5 “ቢነገራችሁም እንኳ፣
የማታምኑትን እናንተን፣
በዘመናችሁ አንድ ነገር ስለማደርግ፣
እነሆ፤ ሕዝቡን እዩ፤ ተመልከቱም፤
እጅግም ተደነቁ።
6 የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣
ምድርን ሁሉ የሚወሩትን፣
ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣
ባቢሎናውያንንአስነሣለሁ።
7 እነርሱም የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤
ፍርዳቸውና ክብራቸው፣
ከራሳቸው ይወጣል።
8 ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣
ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው።
ፈረሰኞቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤
ከሩቅ ስፍራም ይመጣሉ።
ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኵል አሞራ ይበራሉ፤
9 ሁሉም ለዐመፅ ታጥቀው ይመጣሉ።
ሰራዊታቸውእንደ ምድረ በዳ ነፋስ ወደ ፊት ይገሠግሣል፤
ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል።
10 ነገሥታትን ይንቃል፤
በገዦችም ላይ ያፌዛል፤
በምሽግ ሁሉ ላይ ይሥቃል፤
የዐፈር ቊልል ሠርቶም ይይዘዋል።
11 ከዚያም በኋላ እንደ ነፋስ ዐልፎ ይሄዳል፤
ጒልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው።
የዕንባቆም ዳግመኛ ማጒረምረም
12 እግዚአብሔርሆይ፤ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን?
የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ እኛ አንሞትም፤
እግዚአብሔርሆይ፤ እንዲፈርዱ ሾመሃቸዋል፤
ዐለት ሆይ፤ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው።
13 ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤
አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤
ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ?
ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣
ለምን ዝም ትላለህ?
14 አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣
ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ።
15 ክፉ ጠላት ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤
በመረቡ ይይዛቸዋል፤
በአሽክላው ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤
በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል።
16 በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤
ምግቡም ሰብቶአል።
ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤
ለአሽክላውም ያጥናል።
17 ታዲያ መረቡን ባለማቋረጥ መጣል፣
ሕዝቦችንስ ያለ ርኅራኄ መግደል አለበትን?