ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ የቀረበ ጥሪ
1 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወርየእግዚአብሔርቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
2 “እግዚአብሔርበአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፤
3 ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ’ ይላልእግዚአብሔርጸባኦት፤ “እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤እግዚአብሔርጸባኦት፤
4 የቀደሙት ነቢያት፣ ‘እግዚአብሔርጸባኦት፣ “ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ’ ይላል በማለት ለአባቶቻችሁ ሰብከው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፤ ይላልእግዚአብሔር።
5 አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን?
6 ለባሪያዎቼ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃልና ሥርዐት በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሰምን?
“እነርሱም ንስሓ ገብተው፤ እንዲህ አሉ፤‘እግዚአብሔርጸባኦት በወሰነው መሠረት፣ ለሥራችንና ለመንገዳችን የሚገባውን አድርጎብናል።’ ”
በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው
7 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣የእግዚአብሔርቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
8 በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ላይ ተቀምጦአል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም መጋላ፣ ሐመርና አንባላይ ፈረሶች ነበሩ።
9 እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ።
ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ።
10 ከዚያም በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው፣ “እነዚህ በምድር ሁሉ እንዲመላለሱእግዚአብሔርየላካቸው ናቸው” ሲል መለሰ።
11 እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረውየእግዚአብሔርመልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት።
12 ከዚያምየእግዚአብሔርመልአክ፣ “እግዚአብሔርጸባኦት ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ።
13 እግዚአብሔርምከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።
14 ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤
15 ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’
16 “ስለዚህእግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።’
17 “ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤እግዚአብሔርምእንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”
አራቱ ቀንዶችና አራቱ የእጅ ሙያተኞች
18 ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ ከፊቴም አራት ቀንዶችን አየሁ፤
19 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።
እርሱም፣ “እነዚህ ይሁዳን፣ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው” አለኝ።
20 ከዚያምእግዚአብሔርአራት የእጅ ሙያተኞችን አሳየኝ።
21 እኔም፣ “እነዚህስ ምን ሊያደርጉ መጡ?” አልሁ።
እርሱም፣ “እነዚህ ቀንዶች ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እንዳይችል ይሁዳን የበታተኑ ናቸው፤ እነዚህ የእጅ ሙያተኞች ግን የመጡት እነርሱን ሊያስደነግጧቸው፣ ሕዝቡን ለመበታተን በይሁዳ ምድር ላይ ቀንዳቸውን ያነሡትን የእነዚህን የአሕዛብ ቀንዶች ሰብሮ ለመጣል ነው” አለኝ።