ከኀጢአት መንጻት
1 “በዚያ ቀን የዳዊትን ቤትና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከኀጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።
2 “በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላልእግዚአብሔርጸባኦት። “ነቢያትንና ርኵስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
3 ማንም ትንቢት ቢናገር ወላጅ አባትና እናቱ፣ ‘በእግዚአብሔር ስም ሐሰት ተናግረሃልና ሞት ይገባሃል’ ይሉታል። ትንቢት ሲናገርም የገዛ ወላጆቹ ይወጉታል።
4 “በዚያን ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው የትንቢት ራእይ ያፍራል፤ ለማታለልም የነቢያትን ጠጒራም ልብስ አይለብስም።
5 እርሱም፣ ‘እኔ ገበሬ እንጂ ነቢይ አይደለሁም፤ ከልጅነቴጀምሮ ኑሮዬ የተመሠረተውም በዕርሻ ላይ ነው’ ይላል።
6 አንድ ሰው፣ ‘ይህ በሰውነትህላይ ያለው ቊስል ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቀው፣ ‘በባልንጀሮቼ ቤት ሳለሁ የቈሰልሁት ነው’ ይላል።
እረኛው ተመታ፤ በጎቹ ተበተኑ
7 እግዚአብሔርጸባኦት እንዲህ ይላል፤
“ሰይፍ ሆይ፤ በእረኛዬ፣
በቅርብ ወዳጄ ላይ ንቃ!
እረኛውን ምታ፤
በጎቹ ይበተናሉ፤
እኔም ክንዴን ወደ ታናናሾቹ አዞራለሁ።
8 እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፤ “የምድር ሁሉ፣
ሁለት ሦስተኛው ተመትቶ ይጠፋል፤
አንድ ሦስተኛው ግን በውስጡ ይቀራል፤
9 ይህን አንድ ሦስተኛውን ክፍል ወደ እሳት አመጣለሁ፤
እንደ ብር አነጥራቸዋለሁ፤
እንደ ወርቅም እፈትናቸዋለሁ፤
እነርሱ ስሜን ይጠራሉ፤
እኔም እመልስላቸዋለሁ፤
እኔም፣ ‘ሕዝቤ ናቸው’ እላለሁ፤
እነርሱም፣ ‘እግዚአብሔርአምላካችን ነው’ ይላሉ።”