የወርቁ መቅረዝና ሁለቱ የወይራ ዛፎች
1 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም ተመልሶ፣ አንድ ሰው ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አነቃኝ፤
2 እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” አለኝ።
እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ በዐናቱ ላይ የዘይት ማሰሮ ያለበት ሁለንተናው ወርቅ የሆነ መቅረዝ አየሁ፤ በመቅረዙም ላይ ሰባት ቧንቧዎች ያሏቸው ሰባት መብራቶች ነበሩ።
3 ደግሞም አንዱ ከዘይቱ ማሰሮ በስተ ቀኝ፣ ሌላውም በስተ ግራ የሆኑ ሁለት የወይራ ዛፎች አሉ።”
4 ያነጋግረኝ የነበረውንም መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው” አልሁት።
5 እርሱም፣ “ምን እንደሆኑ አታውቅምን?” አለኝ።
እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁት።
6 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለዘሩባቤል የተላከውየእግዚአብሔርቃል ይህ ነው፤ ‘በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም’ ይላልእግዚአብሔርጸባኦት።
7 “ታላቅ ተራራ ሆይ፤ አንተ ምንድን ነህ?በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎች፣ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ፣ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል።”
8 ደግሞምየእግዚአብሔርቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
9 “የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ፤ የሚፈጽሙትም የእርሱ እጆች ናቸው። ከዚያምእግዚአብሔርጸባኦት እኔን ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።
10 “የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? ሰዎች በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ሲያዩ ይደሰታሉ።
“እነዚህ ሰባቱ በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩየእግዚአብሔርዐይኖች ናቸው።”
11 ከዚያም መልአኩን፣ “ከመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉት እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድን ናቸው?” አልሁት።
12 እንደ ገናም፣ “በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ የወርቅ ዘይት የሚያፈሱት እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድን ናቸው?” አልሁት።
13 እርሱም፣ “ምን እንደሆኑ አታውቅምን?” አለኝ።
እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁት።
14 እርሱም፣ “እነዚህ ሁለቱ የምድርን ሁሉ ጌታ ለማገልገል የተቀቡናቸው” አለኝ።