በእስራኤል ጠላቶች ላይ የተወሰነ ፍርድ
1 የእግዚአብሔርቃል ንግር በሴድራክ ምድር ላይ ይወርድበታል፤
በደማስቆም ላይ ያርፍበታል፤
የሰዎችና የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ዐይን፣
በእግዚአብሔርላይዐርፎአልና።
2 ደግሞም በአዋሳኟ በሐማት፣
ጥበበኞች ቢሆኑም እንኳ በጢሮስና በሲዶና ላይ ያርፍባቸዋል።
3 ጢሮስ ለራሷ ምሽግ ሠርታለች፤
ብሩን እንደ ዐፈር
ወርቁንም እንደ መንገድ ላይ ትቢያ ቈልላለች።
4 ጌታ ግን ሀብቷን ይወስዳል፤
በባሕር ያላትንም ኀይል ይደምስሳል፤
እርሷም በእሳት ፈጽማ ትጠፋለች።
5 አስቀሎና አይታ ትርዳለች፤
ጋዛ በሥቃይ ትቃትታለች፤
አቃሮናም እንደዚሁ ትሠቃያለች፤ ተስፋዋ ይመነምናልና።
ጋዛ ንጉሥዋን ታጣለች፤
አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች።
6 ድብልቅ ሕዝቦች አዛጦንን ይይዛሉ፤
የፍልስጥኤማውያንንም ትምክሕት እቈርጣለሁ።
7 ደሙን ከአፋቸው፣
የተከለከለውንም ምግብ ከመንጋጋቸው አወጣለሁ።
የተረፉት ለአምላካችን ይሆናሉ፤
በይሁዳም አለቆች ይሆናሉ፤
አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።
8 እኔ ግን ቤቴን
ከዘራፊ ኀይሎች እጠብቃለሁ፤
ጨቋኝ ከእንግዲህ ሕዝቤን አይወርስም፤
አሁን ነቅቼ እጠብቃለሁና።
የጽዮን ንጉሥ መምጣት
9 አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤
አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤
እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣
ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣
በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ
ወደ አንቺ ይመጣል።
10 ሠረገሎችን ከኤፍሬም፣
የጦር ፈረሶችን ከኢየሩሳሌም እወስዳለሁ፤
የጦርነቱም ቀስት ይሰበራል፤
ሰላምን ለአሕዛብ ያውጃል፤
ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣
ከወንዙምእስከ ምድርዳር ድረስ ይዘረጋል።
11 ለአንቺ ደግሞ፣ ከአንቺ ጋር ከገባሁት የደም ቃል ኪዳን የተነሣ፣
እስረኞችሽን ውሃ ከሌለበት ጒድጓድ ነጻ እለቃቸዋለሁ።
12 እናንት በተስፋ የምትኖሩ እስረኞች፤ ወደ ምሽጎቻችሁ ተመለሱ፤
አሁንም ቢሆን ሁለት ዕጥፍ አድርጌ እንደምመልስላችሁ እናገራለሁ።
13 ቀስቴን እንደ ገተርሁ፣ ይሁዳን እገትረዋለሁ፤
ኤፍሬምንም ፍላጻ አደርገዋለሁ፤
ጽዮን ሆይ፤ ልጆችሽን አስነሣለሁ፤
ግሪክ ሆይ፤ በአንቺ ልጆች ላይ ይነሣሉ፤
እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ።
እግዚአብሔር ይገለጣል
14 እግዚአብሔርበእነርሱ ላይ ይገለጣል፤
ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤
ጌታእግዚአብሔርመለከት ይነፋል፤
በደቡብም ዐውሎ ንፋስ ውስጥ ይጓዛል፤
15 እግዚአብሔርጸባኦትም ይከልላቸዋል፤
ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤
በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ፤
ይጠጣሉ፤ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤
የመሠዊያውን ማእዘኖች ለመርጨት፣
እንደ ተዘጋጀ ዕቃ፣ እነርሱም እንደዚሁ ተሞልተዋል።
16 ሕዝቡን የራሱ መንጋ አድርጎ
በዚያ ቀን አምላካቸውእግዚአብሔርያድናቸዋል።
በአክሊል ላይ እንዳለ ዕንቍ፣
በገዛ ምድሩ ላይ ያብለጨልጫሉ።
17 እንዴት ውብና አስደናቂ ይሆናሉ፤
እህል ጎልማሶችን፣
አዲስ የወይን ጠጅም ቈነጃጅትን ያሳምራል።