ዳንኤል 9

የዳንኤል ጸሎት

1 የሜዶናዊው የአርጤክስስልጅ ዳርዮስ በባቢሎንበነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣

2 በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ለኤርምያስ በተሰጠውየእግዚአብሔርቃል መሠረት፣ የኢየሩሳሌም መፈራረስ ሰባ ዓመት እንደሚቈይ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ።

3 ስለዚህ ማቅ ለብሼ፣ በራሴም ላይ ዐመድ ነስንሼ፣ በጾምና በጸሎት፣ በምልጃም ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ።

4 ወደ አምላኬ ወደእግዚአብሔርእንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ተናዘዝሁም፤

“ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤

5 እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል።

6 ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።

7 “ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን እኛን በበተንህባቸው አገሮች ሁሉ የምንገኝ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምና የመላው እስራኤል ሕዝብ፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለን በዚህ ቀን በኀፍረት ተከናንበናል።

8 እግዚአብሔርሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል።

9 ምንም እንኳ በእርሱ ላይ ያመፅን ብንሆን፣ ጌታ አምላካችን ይቅር ባይና መሓሪ ነው።

10 እግዚአብሔርአምላካችንን አልታዘዝነውም፤ ደግሞም በአገልጋዮቹ በነቢያት በኩል የሰጠንን ሕግ አልጠበቅንም፤

11 መላው እስራኤል አንተን ባለመታዘዝ ሕግህን ተላልፎአል፤ ዘወርም ብሎአል።

“በአንተ ላይ ኀጢአትን ስለ ሠራን፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሓላና ርግማን ፈሰሰብን።

12 ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ በማምጣት፣ በእኛና በገዦቻችን ላይ የተነገረውን ቃል ፈጸምህብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገውን የሚያህል ከሰማይ በታች ከቶ የለም።

13 በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈው፣ ይህ ሁሉ ጥፋት በእኛ ላይ ደረሰ፤ ሆኖም ከኀጢአታችን በመመለስና እውነትህን በመከተል ከአምላካችንከእግዚአብሔርምሕረትን አልፈለግንም

14 አምላካችንእግዚአብሔርበሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ በእኛ ላይእግዚአብሔርጥፋት ከማምጣት አልተመለሰም፤ እኛም አልታዘዝነውም።

15 “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በብርቱ እጅ ያወጣህ፣ እስከዚህም ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግህ፣ ጌታ አምላካችን ሆይ፤ እኛ ኀጢአትን ሠርተናል፤ አንተንም በድለናል።

16 ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቊጣህን መልስ፤ በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል።

17 “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ።

18 አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው።

19 ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”

ሰባው ሱባዔ

20 እኔም እየተናገርሁና እየጸለይሁ፣ የራሴንና የሕዝቤን የእስራኤልን ኀጢአት እየተናዘዝሁ፣ ስለ ቅዱስ ተራራውምእግዚአብሔርአምላኬን እየለመንሁ፤

21 እየጸለይሁም ሳለሁ፣ በመጀመሪያው ራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል፣ በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ በፍጥነት እየበረረ ወደ እኔ መጣ።

22 እርሱም እንዲህ ብሎ አስረዳኝ፤ “ዳንኤል ሆይ፤ አሁን ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ መጥቻለሁ።

23 አንተ እጅግ የተወደድህ ስለ ሆንህ፣ ገና መጸለይ ስትጀምር መልስ ተሰጥቶአል፤ እኔም ይህን ልነግርህ መጣሁ። ስለዚህ መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል።

24 “ዐመፃን ለማስቆም፣ ኀጢአትን ለማስወገድ፣በደልን ለማስተሰረይ፣ ዘላለማዊ ጽድቅን ለማምጣት፣ ራእይንና ትንቢትን ለማተምና፣ እጅግ ቅዱስ የሆነውንለመቀባት ስለ ሕዝብህና ስለ ተቀደሰችው ከተማህ ሰባ ሱባዔታውጇል።

25 “ይህንን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕእስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል። ኢየሩሳሌም ከጐዳናዎቿና ከቅጥሮቿ ጋር ትታደሳለች፤ ይህ የሚሆነው ግን በመከራ ጊዜ ነው።

26 ከሥልሳ ሁለቱ ሱባዔ በኋላ መሲሑ ይገደላል፤ ምንም አይቀረውም። የሚመጣው አለቃ ሰዎችም፣ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ይደመስሳል። ፍጻሜውም እንደ ጐርፍ ይመጣል፤ ጦርነት እስከ መጨረሻው ይቀጥላል፤ ጥፋትም ታውጆአል።

27 አለቃው ከብዙዎች ጋር ለአንድ ሱባዔቃል ኪዳኑን ያጸናል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕትና ቍርባን ማቅረብን ያስቀራል። የታወጀው ፍርድ በእርሱ ላይ እስኪፈስ ድረስ፣ ጥፋትን የሚያመጣ የጥፋት ርኵሰት በቤተ መቅደሱ ውስጥያቆማል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *