መዝሙር 11

የጻድቃን ትምክሕት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር

1 በእግዚአብሔርታምኛለሁ፤

ታዲያ ነፍሴን፣ “እንደ ወፍ ወደ ተራራ ብረሪ”

ለምን ትሏታላችሁ?

2 ደግሞም ለምን እንዲህ ትሉኛላችሁ?

“ክፉዎች፣ እነሆ፣ ቀስታቸውን ገትረዋል፤

የቅኑን ሰው ልብ በጨለማ ለመንደፍ፣

ፍላጻቸውን በአውታሩ ላይ ደግነዋል።

3 መሠረቱ ከተናደ፣

ጻድቅ ምን ማድረግ ይችላል?”

4 እግዚአብሔርበተቀደሰ መቅደሱ አለ፤

የእግዚአብሔርዙፋን በሰማይ ነው።

ዐይኖቹ ሰዎችን ይመለከታሉ፤

ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።

5 እግዚአብሔርጻድቁንና ኀጥኡን ይመረምራል፤

ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣

ነፍሱ ትጠላቸዋለች።

6 እርሱ በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምና ዲን ያዘንባል፤

የጽዋቸውም ዕጣ ፈንታ፣

የሚለበልብ ዐውሎ ነፋስ ነው።

7 እግዚአብሔርጻድቅ ነውና፤

የጽድቅ ሥራም ይወዳል፤

ቅኖችም ፊቱን ያያሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *