የጧት ጸሎት
ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዘመር፣ የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔርሆይ፤ ቃሌን አድምጥ፤
መቃተቴንም ቸል አትበል።
2 ንጉሤና አምላኬ ሆይ፤
ወደ አንተ እጸልያለሁና፣
ድረስልኝ ብዬ ስጮህ ስማኝ።
3 እግዚአብሔርሆይ፤ በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፤
በማለዳ ልመናዬን በፊትህ አቀርባለሁ፤
ፈቃድህንም በጥሞና እጠባበቃለሁ፤
4 አንተ በክፋት ደስ የምትሰኝ አምላክ አይደለህም፤
ክፉም ከአንተ ጋር አያድርም።
5 እብሪተኞች በፊትህ መቆም አይችሉም፤
ክፉ አድራጊዎችንም ሁሉ ጠላህ።
6 ሐሰት የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤
ደም የተጠሙትንና አታላዮችን፣
እግዚአብሔርይጸየፋቸዋል።
7 እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት
ወደ ቤትህ እገባለሁ፤
አንተንም በመፍራት፣
ወደ ተቀደሰው መቅደስህ እሰግዳለሁ።
8 እግዚአብሔርሆይ፤ ከጠላቶቼ የተነሣ፣
በጽድቅህ ምራኝ፤
መንገድህንም በፊቴ አቅናልኝ።
9 በንግግራቸው ውስጥ እውነት የለም፤
ልባቸው የጥፋት ጐሬ ነው፤
ጒሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤
በምላሳቸውም ይሸነግላሉ።
10 አምላክ ሆይ፤ የእጃቸውን ስጣቸው!
ተንኰላቸው መውደቂያቸው ይሁን፤
ከኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ አስወግዳቸው፣
በአንተ ላይ ዐምፀዋልና።
11 አንተን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ደስ ይበላቸው፤
ዘላለም በደስታ ይዘምሩ፤
ስምህን የሚወዱ በአንተ ደስ እንዲላቸው፣
ተከላካይ ሁንላቸው።
12 እግዚአብሔርሆይ፤ አንተ ጻድቃንን ትባርካቸዋለህ፤
በሞገስህም እንደ ጋሻ ትከልላቸዋለህ።