በስደት ጊዜ የጻድቁ ሰው ጸሎት
ዳዊት በብንያማዊው በኩዝ ምክንያት
ለእግዚአብሔር
የዘመረው መዝሙር
1 እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤
ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝ፤ ታደገኝም፤
2 አለበለዚያ እንደ አንበሳ ይዘነጣጥሉኛል፤
የሚያድነኝ በሌለበትም ይቦጫጭቁኛል።
3 እግዚአብሔርአምላኬ ሆይ፤ ይህን አድርጌ ከሆነ፣
በደልም በእጄ ከተገኘ፣
4 በጎ ለዋለልኝ ክፉ መልሼ ብሆን፣
ጠላቴንም በከንቱ ዘርፌ ከሆነ፣
5 ጠላቴ አሳዶ ይያዘኝ፤
ሕይወቴን ከምድር ይቀላቅል፤
ክብሬንም ከዐፈር ይደባልቅ።ሴላ
6 እግዚአብሔርሆይ፤ በመዓትህ ተነሥ፤
በቍጣ በተነሡብኝ ላይ ተነሥ፤
አምላኬ ሆይ፤ ንቃ፤ ትእዛዝም አስተላልፍ!
7 የሕዝቦች ጉባኤ ይክበብህ፤
አንተም ከላይ ሆነህ ግዛቸው፤
8 እግዚአብሔርበሕዝቦች ላይ ይፈርዳል።
እግዚአብሔርሆይ፤ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፤
ልዑል ሆይ፤ እንደ ቅን አካሄዴ መልስልኝ።
9 ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣
ጻድቅ አምላክ ሆይ፤
የክፉዎችን ዐመፅ አጥፋ፤
ጻድቁን ግን አጽና።
10 ጋሻዬልዑል አምላክ ነው፤
እርሱ ልበ ቅኖችን ያድናቸዋል።
11 እግዚአብሔር ጻድቅ ዳኛ ነው፤
ቍጣውንም በየዕለቱ የሚገልጥ አምላክ ነው።
12 ሰው በንስሓ የማይመለስ ከሆነ ግን፣
ሰይፉንይስላል፤
ቀስቱን ይገትራል።
13 የሚገድሉ ጦር ዕቃዎቹን አሰናድቶአል፤
የሚንበለበሉትን ፍላጻዎቹንም አዘጋጅቶአል።
14 ክፋትን እያማጠ ያለ ሰው፣
ቅጥፈትን አርግዞ፣ ሐሰትን ይወልዳል።
15 ጒድጓድ ምሶ ዐፈሩን የሚያወጣ፣
ባዘጋጀው ጒድጓድ ራሱ ይገባበታል።
16 ተንኰሉ ወደ ራሱ ይመለሳል፤
ዐመፃውም በገዛ ዐናቱ ላይ ይወርዳል።
17 ስለ ጽድቁለእግዚአብሔርምስጋና አቀርባለሁ፤
የልዑልእግዚአብሔርንስም በመዝሙር አወድሳለሁ።