ኢያሱ 2

ረዓብና እስራኤላውያን ሰላዮች

1 ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ ምድሪቱን፣ በተለይም የኢያሪኮን ከተማ ሰልሉ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ፤ ሰዎቹም ሄደው ረዓብ ከተባለች ጋለ ሞታቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ።

2 ለኢያሪኮም ንጉሥ፣ “እነሆ፤ ምድሪቱን ሊሰልሉ ጥቂት እስራኤላውያን በሌሊት ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው።

3 የኢያሪኮም ንጉሥ፣ “ወደ አንቺ መጥተው ወደ ቤትሽ የገቡት ሰዎች ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ስለ ሆነ፣ እንድታስወጪአቸው” የሚል መልእክት ወደ ረዓብ ላከ።

4 ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር፣ እንዲህ አለች፤ “በእርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም።

5 ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።”

6 ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር።

7 ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፣ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ።

8 ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣

9 እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔርይህችን ምድር እንደሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ።

10 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜእግዚአብሔርቀይ ባሕርንበፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውንሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል።

11 ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤እግዚአብሔርአምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና።

12 እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩበእግዚአብሔርማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤

13 የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን እንዲሁም የእነርሱ የሆነውን ነፍስ ሁሉ እንድታተርፉልኝ፤ ከሞትም አድኑን።”

14 ሰዎቹም፣ “የእናንተን ሞት ለእኛ ያድርገው! እኛ የምናደርገውን ሁሉ ካልተናገራችሁ፣እግዚአብሔርምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ፣ በጎነትና ታማኝነት እናሳይሻለን” አሏት።

15 መኖሪያ ቤቷ የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ስለ ነበር፣ ሰዎቹን በመስኮት አሾልካ በገመድ አወረደቻቸው።

16 እርሷም፣ “የሚከታተሏችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ፣ ወደ ኰረብታዎቹ ሂዱ፤ እነርሱ እስኪመለሱም ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተሸሸጉ፤ ከዚያ በኋላ መንገዳችሁን ትቀጥላላችሁ” አለቻቸው።

17 ሰዎቹም እንዲህ አሏት፤ “ባማልሽን በዚህ መሓላ የምንያዘው፣

18 ወደ ምድሪቱ በገባን ጊዜ፣ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረ ድሽበት መስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽው፣ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፣ ወንድሞችሽንና የአባትሽን ቤተ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ብቻ ነው።

19 ማንም ከቤትሽ ወጥቶ መንገድ ላይ ቢገኝ፣ ደሙ በራሱ ላይ ነው፤ እኛ አንጠየቅበትም፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር እቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከተነካ የደሙ ባለ ዕዳ እኛ እንሆናለን።

20 እኛ የምናደርገውን ብትናገሪ ግን፣ ካስማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።”

21 እርሷም፣ “ይሁን፤ ባላችሁት ተስማምቻለሁ” ስትል መለሰች፤ ከዚያም ሰደደቻቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀይ ፈትሉንም በመስኮቷ ላይ አንጠለጠለችው።

22 እነርሱም ወጥተው ወደ ኰረብቶቹ ሄዱ፤ የሚከታተሏቸውም ሰዎች በየመንገዱ ሁሉ ላይ ፈልገውና አጥተው እስኪመለሱ ድረስ፣ ሦስት ቀን በዚያው ተሸሸጉ።

23 ሁለቱም ሰላዮች ተመለሱ፤ ከኰረብቶቹም ወርደው ወንዙን በመሻገር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጥተው ያጋጠማቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት።

24 ለኢያሱም፣ “በእርግጥእግዚአብሔርምድሪቱን በሙሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ በዚያ የሚኖረውም ሕዝብ ሁሉ እኛን ከመፍራቱ የተነሣ ልቡ መቅለጡን አይተናል” አሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *