እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ተሻገሩ
1 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ ከእስራኤላውያንም ሁሉ ጋር ከሰጢም ወደ ዮርዳኖስ መጥተው፣ ወንዙን ከመሻገራቸው በፊት በዚያ ሰፈሩ።
2 ከሦስት ቀን በኋላም የጦሩ አለቆች በሰፈር ውስጥ አለፉ፤
3 ሕዝቡንም እንዲህ ሲሉ አዘዙ፤ “ሌዋውያን ካህናቱ የአምላካችሁንየእግዚአብሔርንየቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ስታዩ፣ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ታቦቱን ተከተሉ፤
4 ካሁን በፊት በዚህ መንገድ ሄዳችሁ ስለማታውቁ፤ በየት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ በዚህ ትረዳላችሁ፤ ሆኖም በታቦቱና በእናንተ መካከል የሁለት ሺህ ክንድያህል ርቀት ይኑር፤ ወደ ታቦቱም አትቅረቡ።”
5 ከዚያም ኢያሱ ሕዝቡን፣ “በነገው ዕለትእግዚአብሔርበመካከላችሁ አስደናቂ ነገር ስለሚያደርግ ራሳችሁን ቀድሱ” አላቸው።
6 ኢያሱም ካህናቱን፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ ሕዝቡን ቀድማችሁ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡን ቀድመው ሄዱ።
7 እግዚአብሔርምኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ፣ በእስራኤል ሁሉ ፊት አንተን ከፍ ከፍ ማድረጌን በዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ።
8 የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትንም ካህናት፣ ‘ከዮርዳኖስ ውሃ ዳር ስትደርሱ፣ በወንዙ ውስጥ ገብታችሁ ቁሙ’ በላቸው።”
9 ኢያሱ የእስራኤልን ሕዝብ “ወደዚህ ቀርባችሁ፣ የአምላካችሁንየእግዚአብሔርንቃል ስሙ አላቸው፤
10 እንግዲህ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ መሆኑንና እርሱም በእርግጥ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ኤዊያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ እንዴት አድርጎ እንደሚያሳድዳቸው የምታውቁት በዚህ ነው።
11 እነሆ፤ የምድር ሁሉ ጌታ የቃል ኪዳኑ ታቦት ቀድሞአችሁ ወደ ዮርዳኖስ ይገባል።
12 እንግዲህ ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰው ምረጡ፤ ከየነገዱም አንዳንድ ሰው ይሁን።
13 የምድርን ሁሉ ጌታየእግዚአብሔርንታቦት የተሸከሙት ካህናት ገና እግራቸውን በዮርዳኖስ ውሃ ውስጥ እንዳስ ገቡ፣ ቊልቊል የሚወርደው ውሃ ወዲያውኑ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል።”
14 ስለዚህ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ሰፈሩን ለቀው ሲወጡ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከፊታቸው ቀድመው ሄዱ።
15 ወቅቱም የመከር ጊዜ በመሆኑ፣ የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ነበር፤ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣
16 ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ “አዳም” ተብላ እስከምትጠራው ሩቅ ከተማ ድረስ በመከማቸት እንደ ክምር ተቈለለ፤ ቊልቊል ወደ ዓረባ ጨው ባሕርየሚወርደውም ውሃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም ከኢያሪኮ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ተሻገሩ።
17 የእግዚአብሔርንየቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናትም፣ ሕዝቡ ሁሉ ማለት እስራኤል በሙሉ ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቁ ምድር ላይ ቀጥ ብለው ቆመው ነበር።