ኢያሱ 7

የአካን ኀጢአት

1 እስራኤላውያን ግን እርም የሆነውን ነገርለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪልጅ፣ የዛራ ልጅ እርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደየእግዚአብሔርቊጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።

2 ኢያሱ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ካለችው ከቤት አዌን አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጋይ ከኢያሪኮ ሰዎችን ልኮ፣ “ወደዚያ ውጡ፤ አገሪቱንም ሰልሉ” አላቸው፤ ሰዎቹም ወጥተው ጋይን ሰለሉ።

3 ወደ ኢያሱም ተመልሰው፣ “ጋይን ለመውጋት ሕዝቡ ሁሉ መሄድ አያስፈልገውም፤ በዚያ ያለው ሕዝብ ጥቂት ስለ ሆነ፣ ከተማዪቱን ለመውጋት ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰው ስለሚበቃ ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ በመሄድ አይድከም” አሉት።

4 ስለዚህ ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጣ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሸ፤

5 የጋይም ሰዎች እስራኤላውያንንም ከከተማዪቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሽባሪምድረስ በማባረር ቊልቊለቱ ላይ መቷቸው፤ ከእነርሱም ሠላሳ ስድስት ያህል ሰው ገደሉባቸው። ከዚህ የተነሣም የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውሃም ፈሰሰ።

6 በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፋ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንደዚሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።

7 ኢያሱም እንዲህ አለ፤ “ወዮ! ልዑልእግዚአብሔርሆይ፤ ዮርዳኖስን አሻግረህ ይህን ሕዝብ ወደዚህ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንዲያጠፉን ነውን? ምነው ሳንሻገር እዚያው ማዶ በቀረን ኖሮ!

8 ጌታ ሆይ፤ እስራኤል በጠላቱ ፊት ሲሸሽ እኔ ምን ልበል?

9 ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?”

10 እግዚአብሔርኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ?

11 እስራኤል በድሎአል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ እርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋር ደባልቀዋል።

12 እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም።

13 “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ እርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ።

14 “ ‘ማለዳ በየነገድ በየነገዳችሁ ሆናችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ይወጣል፤ እንዲሁምእግዚአብሔርየሚለየው ጐሣ በየቤተ ሰቡ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል፤እግዚአብሔርየሚለየው ቤተ ሰብ ደግሞ በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል።

15 እርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤የእግዚአብሔርንቃል ኪዳን አፍርሶአል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞአልና።”

16 በማግሥቱ ጥዋት ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ እስራኤልንም በየነገድ በየነገዳቸው ሆነው እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ተለየ፤

17 የይሁዳንም ጐሣዎች ወደ ፊት አቀረበ፤ ከእነዚህም የዛራን ጐሣ ለየ፤ እነዚህን ደግሞ በየቤተ ሰባቸው እንዲወጡ አደረገ፤ ከእነዚህም ዘንበሪ ተለየ።

18 ኢያሱ የዘንበሪን ቤተ ሰብ አባላት አንድ በአንድ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የሆነውም የዛራ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የከርሚ ልጅ አካን ለብቻው ተለየ።

19 ኢያሱም አካንን፣ “ልጄ ሆይ፤ ለእስራኤል አምላክለእግዚአብሔርክብርን ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውን ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው።

20 አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክእግዚአብሔርንበድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤

21 ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖርየመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅልብርናክብደቱ አምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሮአል።”

22 በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ።

23 ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተውበእግዚአብሔርፊት አኖሩ።

24 ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋር ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ።

25 ኢያሱም፣ “እንዲህ ያለውን መከራ ለምን አመጣብህን? እነሆ፤ ዛሬ በአንተም ላይእግዚአብሔርመከራ ያመጣብሃል” አለው።

ከዚያም እስራኤል በሙሉ በድንጋይ ወገሩት፤ የቀሩትንም እንደዚሁ ከወገሩ በኋላ በእሳት አቃጠሏቸው።

26 በአካንም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታየውን ታላቅ የድንጋይ ቊልል ከመሩበት፤ ከዚያምእግዚአብሔርከአስፈሪ ቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያ ስፍራ የአኮርሸለቆ ተባለ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *